ወቅታዊ መግለጫ‹‹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ የሚኖር...

‹‹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት ህጋዊ ስርአትን የተከተለ ሊሆን ይገባል፤ ››

ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/

(ጥቅምት 12 2016 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፤

ምክር ቤታችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ላይ ከህግ አግባብ ውጪ አስሮ የማቆየትና ለስርጭት የተዘጋጀ የህትመት ውጤትን የማገድ ድርጊቶች እንደተፈፀመባቸውና በዚህም ሳቢያ ተቋማቱ የእለት ተዕለት ስራዎቻቸውን ለመስራት መቸገራቸውን ከደረሱት ሪፖርቶች ተገንዝቧል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 4 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው ‹ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፤ሃሳቦች፤አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው በሕግ ጥበቃ ይደረግለታል› ይላል፡፡ ሆኖም ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ጥበቃ ለማድረግ የወጡ የሕግ ድንጋጌዎች ቢኖሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገሪቱ ህግ መሠረት ተመዝግበውና ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋዜጠኞችና የህትመት ውጤት በፀጥታ ሃይሎች ከህገ አግባብ ውጪ መታገታቸው ምክር ቤታችንን አሳስቦታል፡፡

እንደ አብነትም በኢትዮ ሃበሻ አሳታሚ ድርጅት በየሳምንቱ እየታተመ የሚሰራጨው ጊዮን መፅሄትና ዋና አዘጋጁ ነሃሴ 19 ቀን 2015 በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ከአንድ ሳምንት በሃላ ዋና አዘጋጁ ያለ ክስ ሲለቀቅ መፅሄቱ ከአንድ ወር ከ 15 ቀን በላይ አልተለቀቀም፤ የትርታ ኤፍ ኤም 97 7 የፕሮግራም ዳይሬክተርም ጳጉሜ 5 ቀን 2015 ከመኖሪያ ቤቱ በጥፀታ ሃይሎች ከተወሰደ በሃላ ከአንድ ወር ከ20 ቀናት በላይ ክስም አልተመሰረተበትም፤ፍርድ ቤትም ሊቀርብ አልቻለም፤

በመናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238 አንቀጽ 85 /7 ላይ በግልጽ እንደተደነገገው በየጊዜው የሚወጣ ህትመት ከመሰራጨቱ በፊት በጽጥታ አካላት የሚሰጥ የእገድ ትዕዛዝ የትዕዛዙ መነሻ የሆነውን አንቀጽ ወይም አንቀጾች፣ የህትመቱን ቅፅ፣ ጽሁፉ የወጣበትን እትም መገለጽ አለበት፡፡ እገዳውም ለሥርጭት በተዘጋጁ ህትመቶች ላይ ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡> ሲል ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ጊዮን መጽሄት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ በአዋጁ መሰረት ተመርምሮ የጋረጠው አደጋ ስለመኖሩ ያልተረጋገጠ ሲሆን ለፍርድ ቤትም በ48 ሰአት ውስጥ የቀረበ ክስ የለም፡፡

በሌላ በኩል በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈፀም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ-ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ 1238/13 አንቀፅ 86 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ ቢደነገግም የትርታ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ግን ከአዋጁ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለሳምንታት ያለ ክስ በእስር ላይ ይገኛል።

የወንጀል ድርጊቶች ከመፈፀማቸው በፊት መከላከል ተፈፅሞ ሲገኝም አፋጣኝ ፍትሐዊ እርምጃዎችን በህግ አግባብ የመውሰድ ህገ መንግስታዊ ግዴታ የተጣለባቸው የፀጥታ አካላት ጋዜጠኞችን አስሮ መረጃ መሰብሰብና አስሮ ለቀናት ክስ አለመመስረት እንዲሁም የህትመት ውጤትን ከስርጭት ማገድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ስራቸውን በነጻነት እንዳያከናውኑ የሚያስተጓጉል ተግባር ነው፡፡ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቀማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት በህጉ አግባብ ብቻ መከናወን ይኖርበታል ብለን እናምናለን፤ ይህ እለመሆኑ ግን ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገፀታ ላይ ጥላ የሚያጠላ ሆናል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት የፍትህ አካሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ያለ ቢሆንም ጋዜጠኞችንና ተቋማቱን በተመለከተ በሕጉ አግባብ ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ያለመቻሉ ምክር ቤታችንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ችግሩ እንዲፈታም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ጉዳዩን በማሳወቅ ክትትል እያደረገ ነው፡፡

በመሆኑም መንግስት የወንጀል ተግባሮችን የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ላይ የሚፈፀሙ የመብት ጥስቶችን በህጉ አግባብ ብቻ እንዲመራ በማድረግ ህገ ወጥ የወንጀል ድርጊቶችን በተቻለ ፍጥነት በማረም ሕገመንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤

ጥቅምት 12 ቀን 2016 አዲስ አበባ፤

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe