ወቅታዊ መግለጫ‹መገናኛ ብዙሃን ኃይማኖታዊ ጉዳዮችን ከፍ ባለ የኃላፊነት ስሜትና ሥነ ምግባርን ባከበረ መልኩ...

‹መገናኛ ብዙሃን ኃይማኖታዊ ጉዳዮችን ከፍ ባለ የኃላፊነት ስሜትና ሥነ ምግባርን ባከበረ መልኩ ሊዘግቡ ይገባል›

ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/

(ጥር 302015 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ ከ60 በላይ የህዝብ ፤የግል ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ  የመገናኛ ብዙሃን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የውስጥ ችግር ጋር በተያያዘ እያሰራጩት ያሉት ዘገባ  ከተጨባጩ እውነታ ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን ከትክክለኛ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ጋር የሚጋጭ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በተለይም አንዳንድ  ኃይማኖታዊ መገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ሚዲያ ተዋንያን  የራስን ኃይማኖታዊ አስተምህሮትና መንፈሳዊ መልዕክቶችን ከማስተማር ይልቅ እያሰራጩት ያሉት መልዕክት ህዝብን የሚያሸብርና ስጋት ላይ የሚጥል  ከመሆኑም በላይ ሀገሪቱን የእርስ በእርስ ግጭት ማዕከል አድርጎ የማቅረብ ዝንባሌ እንደሚስዋባቸው ታዝበናል፤

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/13 አንቀፅ 70 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው ማንኛውም ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራም በሃይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳት፣ የሌሎችን ሃይማኖት ወይም እምነት ማንኳሰስ፣ ወይም በሃይማኖት ተከታዮች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀሰቀስ እንደማይፈቀድ ተደንግጓል፡፡በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራሞችን በሚያሰራጩበት ወቅት በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በሃላፊነት መንፈስ እንዲሁም ከፍ ባለ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር በመመራት  ሊሆን ይገባል፡፡

በተለይም ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምዝገባ ያከናወኑ የሃይማኖት ብሮድካስት ባለፈቃዶች ሃይማኖታዊ አስተምህሮታቸውን፣ የፀሎት መርሃ ግብሮቻቸውን፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን የማከናወን፣ ስነ-ምግባር የማነፅና የማስተማር፣ሃይማኖታዊ ተግባራቸውን በነፃነት የሚያራምዱበትን ምህዳር የመፍጠር እና ለተከታዮቻቸው ተደራሽ የመሆን መብት ያላቸው ቢሆንም የሌሎች ኃይማኖቶችን አስተምህሮና የእምነት ምሶሶ ማጥላላት፤  የዜጎችን መቻቻልና አብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ፤ ሁከትና ግጭት የሚጋብዙ እና በግለሰቦችና በማኅበረሰቦች ላይ አካላዊ ጥቃት እንዲፈፀም የሚያነሳሱ መሆን የለባቸውም፤

በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን ለዘመናት አብሮ በኖረው ህዝብ መሀል የሚያሰራጩት  ኃይማኖት ነክ መረጃዎች ከጥላቻ ንግግሮችና ቅስቀሳዎች የፀዱ እንዲሆኑ ሰባኪያንንና የኃይማኖቱ ተከታዮችን ማንቃት እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ ማስጨበጥ  ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ተቋማት ብዙ ይጠበቃልና የስነ ምግባር ደንቡን አክብረው ሊሰሩ ይገባል ፡፡ ካለፉት ችግሮቻችን ተምረን ለተሻለ የሀገር ሰላም ግንባታ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች  በጋራ ሊቆሙ ይገባል፡፡

በመጨረሻም መንግስት ኃይማኖትን መሠረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶች ማብቂያ ወደሌለው ሁከት ሊያመራ ስለሚችል የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሕገ መንግስታዊ ግዴታውን በኃላፊነት ስሜት ሊወጣ ይገባል እንላለን፡፡

 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ጥር 30 ቀን 2015 አዲስ አበባ፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe