አዲስ አበባ፡ ጥር 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ፡፡ የምክር ቤቱ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳዲስ አባላትን ማጽደቅ እና የምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብን ማሻሻያ ማድረግ በጉባኤው የሚነሱ ሐሳቦች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በጉባዔው ላይ እንደተነሳው መገናኛ ብዙኃን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ተግባራት እንዲሳለጡ ትልቅ አስተዋጾኦ ያበረክታሉ፤ የሐሰት መረጃዎችን በማጋለጥ ወደ ማኅበረሰቡ እውነተኛ መረጃን በማድረስ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ተጠቅሷል፡፡
መገናኛ ብዙኃን በነጻነት እና ገለልተኛ ኾነው እንዲሠሩ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ትልቅ ሚና እንደሚጫዎት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ተናግረዋል።
አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ከሥነ ምግባር የራቁ ተግባራትን ስለሚፈጽሙ ምክር ቤቱ መገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች በሕግ አግባብ እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ መገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች በሕጉ መሰረት ሥራቸውን ገለልተኛ በመሆን እንዲሠሩ እና ፖለቲከኞች መገናኛ ብዙኃንን የፖለቲካ ተፅዕኖ መፍጠሪያ እንዳያደርጓቸው ማድረግ እንደሚገባውም ተመላክቷል፡፡