ሌሎችፓርላማው የተጣሰውን ሕግ ያስከብር!

ፓርላማው የተጣሰውን ሕግ ያስከብር!

የሕግ የበላይነት በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ ሕግ ተርጓሚ አካሉ (የዳኝነት) እና ሕግ አውጭው ፓርላማ አገር በሥርዓት እንዲመራ የሚጠቀሙበት መሣሪያ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት የመንግሥት አካላት እየተናበቡና የእርስ በርስ ቁጥጥር እያደረጉ ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ አገረ መንግሥቱ የተረጋጋና ሰላማዊ ይሆናል፡፡ በተቃራኒው ከሆነ ደግሞ ለሕገወጥነት በር ይከፈትና ሰላምና መረጋጋት ይደፈርሳል፡፡ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች መሆናቸውንና ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለህሊናቸው ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ ለፌዴራል መንግሥት በተሰጠው የሥልጣን ክልል ውስጥ ሕጎችን እንደሚያወጣም ተደንግጓል፡፡ ፓርላማው ሕግ አውጭ አካል በመሆኑ ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከተለያዩ ሕጎች ጋር የሚጋጩ አሠራሮች ሲኖሩ፣ የማስቆም ወይም የማገድ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን መወጣት ከተሳነው ግን በአገሪቱ ውስጥ ማናለብኝነት ይንሰራፋል፡፡

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሠረት ለፓርላማው ቀርቦ መፅደቅ የነበረበት የቦርድ አባላት ሹመት፣ የአዋጁን መሠረታዊ የሚባሉ ድንጋጌዎች ከመጣሱም በላይ ድጋፍ የሰጡ የምክር ቤት አባላት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ፓርላማውም ከአዋጁ መሠረታዊ መርሆ ባፈነገጠ አሠራር እንዲፀድቅ ማድረጉም አጠያያቂ ነው፡፡ የቦርድ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሰየሙ፣ እነሱን የመመልመልና ሹመታቸውን የማፀደቅ ሒደቱ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት፣ ሕዝብም ዕጩዎችን ለመጠቆምና አስተያየት ለመስጠት ዕድል እንደሚሰጠው፣ የዕጩዎች አመራረጥ ሒደትና የተመረጡ ዕጩዎች ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ይፋ እንደሚደረግ በአዋጁ ውስጥ ተብራርቶ ተደንግጓል፡፡ በአዋጁ በግልጽ እንደተደነገገው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለልተኛ ሆኖ መደራጀት አለበት፡፡ የቦርዱ አባላትም ሥራቸውን ሲያከናውኑ ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነት ወይም ተፅዕኖ ገለልተኛና ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ መሆን እንደሌለባቸውም ተደንግጓል፡፡ ይህም በጥቆማና በምልመላ ሒደት መረጋገጥ ነበረበት፡፡ በአዋጁ ውስጥ አግባብነት ካላቸው የመንግሥት አካላት ሦስት ይካተታሉ ማለት፣ የፓርቲ አባላትን ማለት እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ አባላት ጉዳይ ለሚዲያው ወይም ለባለድርሻ አካላት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ራሱ ሕግ አውጭውን ፓርላማ፣ የዳኝነት አካሉን፣ አስፈጻሚውን መንግሥት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሙሉ፣ የሲቪል ማኅበራትን፣ የዴሞክራቲክ ተቋማትን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን፣ እንዲሁም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉና ሁሉንም ዜጎች ጭምር ስለሚመለከት በፍፁም ሕግ መጣስ የለበትም፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከማናቸውም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ኃላፊነቱን መወጣት የሚችለው፣ የጥቅም ትስስር ወይም ግጭት ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ሥራውን እንዳያውኩት ነው፡፡ ቦርዱ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባራት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እያንዳንዱን ዜጋ የሚመለከቱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የሚያገናኙ ጉዳዮች ደግሞ ነፃነትንና ገለልተኝነትን የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባልም ሆነ ተቀጣሪ በቦርድ አባልነት መሳተፍ የለበትም፡፡ ለዚህም ሲባል የዕጩዎች ጥቆማና ምልመላ ልክ እንደ አገራዊ የምክክር ኮሚሽነሮች ለሕዝብ ግልጽ መሆን ነበረበት፡፡ በአዋጁ ውስጥ የሠፈረው ሒደትም ሆነ መሥፈርት ባለመከበሩ ምክንያት ሕግ ተጥሷል፡፡ ሕግ በአግባቡ ካልተከበረ ደግሞ ለአምባገነንነት በር ይከፈታል፡፡

የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆንና ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት እንደሚችል የተደነገገው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 ነው፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት የያዙ ሰዎችም ሆኑ የምክር ቤት አባላት ሕግ በግላጭ ሲጣስ የማረም ወይም የማስተካከል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ፓርላማውም ሆነ አስፈጻሚው መንግሥት ሥራቸውን ማከናወን ያለባቸው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት ስለሆነ፣ ደግሞ ደጋግሞ ሕግ እንዲያከብሩ ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ የመንግሥት ተሿሚም ሆነ የሕዝብ ተመራጭ ሕግ ማክበር ካልቻለ ወይም በማናለብኝነት አገር እንድትመራ ከፈለገ፣ ስለሕግ የበላይነትም ሆነ በሥርዓት ስለመተዳደር መግባባት አይቻልም፡፡ ሕዝብን በሥርዓት ማስተዳደር ከሚጠበቅበት መንግሥትም ሆነ ፓርላማ የሕግ ጥሰት ሲስተዋል በፍጥነት መታረም አለበት፡፡ ሕግ አውጭው አካልም ሆነ አስፈጻሚው ሕግ ሳያከብሩ፣ ሌሎች እንዲያከብሩ የማድረግ ሞራላዊ ብቃት አይኖራቸውም፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚስተዋሉ ግድያዎችና ማፈናቀሎች፣ ሕግ የማክበርና የማስከበር ፍላጎት አለመኖር ማሳያ መሆናቸውም ሊታወቅ ይገባል፡፡

በመገናኛ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች ይመለከተናል የሚሉ አካላት የቦርድ አባላቱ ሹመት ማፅደቅም ሆነ አጠቃላይ ሒደቱ ትክክል አይደለም ሲሉ፣ የሚመለከታቸው ደግሞ ለእርምት ራሳቸውን ዝግጁ ካላደረጉ ሕግ ማስከበር አይቻልም፡፡ አዋጁን በማርቀቅም ሆነ በማፀደቅ ሒደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸውም ሆኑ በተለያዩ ስብሰባዎች አስተዋፅኦ ያደረጉ ወገኖች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ያለ ምንም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ተደራጅቶ የሚዲያ ተቆጣጣሪነት ሚናውን እንዲወጣ ነበር ሲደክሙ የቆዩት፡፡ ይህ ሁሉ ድካም ተደርጎበት የወጣ አዋጅ ተጥሶ የቦርድ አባላት ሹመት በፓርላማው በዘፈቀደ ሲፀድቅ ሊያስደነግጥ ይገባል፡፡ አሁንም ቢሆን ፓርላማውም ሆነ አስፈጻሚው መንግሥት ይህንን ድርጊት በፍጥነት መግታት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር የነበሩት አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባልነት ሲታጩ፣ ‹‹የጥቅም ግጭት ስለሚፈጠር አልሆንም›› በማለት አርዓያነት ያለው ተግባር መፈጸማቸው አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የሞራል ልዕልና በታየባት አገር ውስጥ፣ ሕግ መጣስ የነውሮች ሁሉ ነውር እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በዚህ መሠረትም ፓርላማው የተጣሰውን ሕግ ያስከብር!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe