የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከጀርመን ዓለማቀፍ የሚዲያ አካዳሚ ጋር በመተባበር ከተለያዩ ሬዲዮ ጣቢያዎች ለተዉጣጡ ጋዜጠኞች በግጭት ተኮር አዘጋገብ እና በሰላም ጋዜጠኝነት ላይ አተክሮ ሲስጥ የቆየው ስልጠና ሰሞኑን ተጠናቀል፡፡
ስልጠናዉ በሶስት ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያዉ የምክር ቤቱ አባላት ከሆኑ የተለያዩ የክልል እና የአዲስ አበባ ሬዲዮ ጣቢያዎች የተዉጣጡ የአመራር አካላት የተሳተፉበት የሁለተኛዉ እና የሶስተኛዉ ምዕራፍ ሰልጣኞች ደግሞ ከነዚሁ ሬዲዮ ጣቢያዎች ለተዉጣጡ የሬዲዮ ሪፖርተሮች፣ አዘጋጆችና ኤዲተሮች የተዘጋጀ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በመጀመሪያዉ የስልጠና ምዕራፍ መከፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተዉ ባስተላለፉት መልዕክት ምክር ቤታችን የተቋቋመበት ዋና ዓላማ እንዲሳካ የአባል ተቋማትን ጋዜጠኞችና የአመራር አካላት አቅም በስልጠና የመደገፍ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ የጀርመን አለማቀፍ የሚዲያ አካዳሚም ሃላፊ ሚስተር ጃስፐር ፋንክ ይኸንኑ ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸዉን ተስፋ ገልፀዋል ፡፡

በነሃሴ ወር 2015 ዓ.ም በመስከረም እና በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም በተለያዩ ሆቴሎች እና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት አዳራሽ የተካሄዱት እነዚህ የ3 ምዕራፍ ስልጠናዎች እያንዳዳቸው አራት አራት ቀናት የተካሄዱ ሲሆን አሰልጣኞቹም በአዉሮፓ በኢሲያ እና በአፍሪካ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የጀርመን አለማቀፍ የሚዲያ አካዳሚ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ባለሙያዎች ናቸው ፡፡
ስልጠናዉ ለሬዲዮ ጋዜጠኞች የተሰጠበት ምክንያት ሬዲዮ የተሻለ ተደራሽነት ያለዉ በመሆኑም ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን የግጭትና ሁከት የማረጋጋት ተልዕኮዓቸዉን በተሻለ ብቃት መወጣት እንዲችሉ አቅማቸዉን መገንባትና ማነቃቃት አስፈላጊ መሆኑን የስልጠናዉ አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡
‹‹መገናኛ ብዙሃን ለሰላም ማስፈን ›› በሚል አብይ ርዕስ የተዘጋጀዉ ይህ ስልጠና ንድፈ ሃሳብን ከተግባር ልምምድና ከሰልጣኞች የስራ ተመክሮ ጋር አስተሳስሮ የተቃኘበት ነበር ፡፡ እናም ከጥቃቅን የግጭት አይነቶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ምን እንደሚመስሉና የጋዜጠኞች ሃላፊነት ምን መሆን እንዳለበት ተቃኝቷል፡፡
ጋዜጠኞች በየሬዲዮ ጣቢያቸው ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ግጭት ተኮር ርዕሰ ጉዳዮች ከመለየትና ከማጤን ጀምሮ በፕሮግራሞቻቸው እንዴት መቃኘት እንዳለባቸው ግንዛቤ ማዳበራቸውን ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

እነዚህ ሰልጣኞች በስልጠናዉ ያገኙትን ግንዛቤ መሰረት የደረገ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን በየጣቢያቸው እንደሚሰሩ የሚጠበቅ ሲሆን ይኸንንም በቀጣይነት አሰልጣኞቹ ጉብኝት በማድረግ የፕሮግራም ዝግጅቶቻቸውን እንደሚመለከቱትና የሙያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ከጠቅላላዉ የስልጠና መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል፡፡
የጀርመኑ አለማአቀፍ የሚዲያ አካዳሚ (IMA) በመገናኛ ብዙሃንና በጋዜጠኝነት ሙያ እንዲሁም ከፕሬስ ነፃነት ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የምርምር የስልጠና እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን የሚያከናዉን በመንግስት የበጀት ድጋፍ የሚደረግለት በአሰራሩ ገለልተኛ የሆነ ተቋም ነው፡፡
አካዳሚ ተቋሙ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት ጋር የጀመረዉን የሙያተኞች የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቃል፡፡