ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/
ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት
የ2016 የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ምክንያት በማድረግ የተሰጠ መግለጫ
‘’ የፕሬስ ነጻነት ቀን ስከበር ጋዜጠኞች ለአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት በትኩረት
ሊሰሩ ይገባል፡፡‘’
(ሚያዝያ 24፤2016 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ ከ80 በላይ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፤
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ አማካይነት በየዓመቱ ሚያዝያ 25 ወይም ሜይ 3 የሚከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በአለም ዙሪያ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ ለመገምገም፣ መገናኛ ብዙሃን በነጻነታቸው ላይ ከሚሰነዘረው ጥቃት ለመከላከል እና ህይወታቸውን ላጡ ጋዜጠኞች ክብር ለመስጠት የሚከበር በመሆኑ የመገናኛ ብዙኃንና የፕሬስ ነፃነት አቀንቃኞች ዕለቱን በተለየ ሁኔታ ይመለከቱታል፡፡
እለቱ በአለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19 ላይ የተመለከተውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማክበር እና ማስከበር እንደሚያስፈልግ መንግስታትን ለማስታወስ የሚከበር ከመሆኑም በላይ ጋዜጠኞች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች፣ እንግልት፣ እስራት እና ሁከትን ለመቀነስ እንዲቻል ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ለመወያየት እና ግንዛቤን ለማስጨበጥ እድል የሚሰጥ ልዩ ቀንም ነው፡፡
የዘንድሮው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ‘’ጋዜጠኝነት በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ውስጥ” ወይም “Journalism in the face of the Environmental Crisis” በሚል መሪ ቃል ሲከበር የፕሬስ ነጻነት መሠረታዊ መርሆዎችን በማጽናት አሁን ካለው ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀውስ አንፃር የጋዜጠኝነት ሙያ አስፈላጊነት ላይ ያተኩራል፡፡
የአየር ንብረት እና የብዝሃ ህይወት ቀውስ በአካባቢ እና ስነ–ምህዳር ላይ ብቻ ሳይሆን በአለም ዙሪያ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት እየጎዳ ነው፤ በዚህም በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ውስጥ ሃገራችን የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ ከመሆንዋም ሌላ ችግሩን ለመቅረፍ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ትገኛለች፡፡
በዚህ ረገድ ባለፉት በርካታ አመታት በሃገራችን ቀላል የማይባሉ ጥረቶች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን በተለይ ባለፉት 5 አመታት የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ጥረቶች ቀላል አይደሉም፡፡ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የሚተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና በየአካባቢው የሚካሄደው የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በሀገራችን ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚህ ውስጥ የሃገራችን መገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ቀላል የማይባል ሚና ተጫውተዋል፡፡
የዘንድሮ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ክብረ በዓልም ጋዜጠኞች የዓለማችንና የአካባቢያችንን ስነ ምህዳር መዛባት ስለሚያስከትለው ችግር ጠንቅቀው በመረዳት ፤ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የበኩላቸውን ሚና በመጫወት እንዲሁም ትክክለኛ መረጃን ለህብረተሰቡ በማድረስ በኩል ያላቸውን የማይተካ ሚና እንዲያጎለብቱ እድል ይፈጥራል፡፡
የሀገራችን መገናኛ ብዙሃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡ አካባቢያዊ ለውጦችን በማጠናከር፣ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ህጐች፣ አሰራሮችና ለአካባቢ ደህንነት ጠንቅ የሆኑ አመለካከቶች ላይ በመወያየት ትኩረት እንዲያገኙ ሲጥሩ ጋዜጠኞች ሥራቸውን ከስጋትና ፍርሃት ነፃ ሆነው በኃላፊነት ስሜት የሚሰሩበት ሁኔታ ትኩረት ሊስጠው እንደሚገባ ምክር ቤታችን ያምናል፡፡
በመሆኑም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ጋዜጠኞች ስለአከባቢ ጉዳዮች፤ ሰለሚያስከትሉት ጉዳትና ስለመፍትሔዎቻቸው ሲዘግቡ ስለ አካባቢ ደህንነት ጥበቃ ወቅታዊና ሁሉን አቀፍ እሳቤ በሚጎላበት መንገድ ሊሆን ይገባል እንላለን፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሁሌም እንደሚለው ጋዜጠኝነት ይበልጥ ሙያውን ያከበረ ስነ ምግባሩን የጠበቀ፤ ጋዜጠኞች ከስጋትና ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ነፃ ሆነው የሚሰሩበት ምህዳር እንዲኖር እንዲሁም ዜጎች ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙበት እሳቤ የሚያጎላበት ቀን ሆኖ በዓሉ እንዲከበር ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት ሁሉም የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
በመጨረሻም የፕሬስ ነጻነት ቀን ስናከብር ጋዜጠኞች ለአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት በትኩረት እንዲሰሩ አደራ እንላለን፡፡
የፕሬስ ነጻነት ቀኑን ስናከብርም ጋዜጠኞች ለአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት የበኩላችንን ሚና በመጫወት መሆን ይኖርበታል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሚያዝያ 24 ቀን 2016 አዲስ አበባ፤