ዜናየግልግል ዳኝነት የአስራር ደንብ መገናኛ ብዙሃን በነፃነትና በተጠያቂነት መርህ እንዲንቀሳቀሱ ጉልህ ሚና...

የግልግል ዳኝነት የአስራር ደንብ መገናኛ ብዙሃን በነፃነትና በተጠያቂነት መርህ እንዲንቀሳቀሱ ጉልህ ሚና ይኖረዋል

ጥር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የግልግል ዳኝነት የአሰራር ደንብ መገናኛ ብዙሃን በነፃነትና በተጠያቂነት መርህ እንዲንቀሳቀሱ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤው የግልግል ዳኝነት የአሰራር ደንብን አጽድቋል። ደንቡ በዋናነት የመገናኛ ብዙሃንንና ጋዜጠኞችን መብት ከማስከበር ባለፈ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባርን አክብረው እንዲሰሩ ያደርጋል።

የምክር ቤቱ የስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ እንዳሉት፤ የግልግል ዳኝነት አሰራር ደንብ ምክር ቤቱ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማስፈፀም ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ድንቡን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል የሰው ሃይልና አስፈላጊው መሰረተ ልማት መሟላቱንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ አንቂነት እና በጋዜጠኝነት መካከል የሚታየው የሙያ መደበላለቅ በጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር  ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡ከዚህ አኳያ ደንቡ ጋዜጠኞች ነፃነታቸውን ጠብቀውና ተጠያቂነትን አክብረው እንዲሰሩ በማድረግ ለሙያው እድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡

ደንቡ ጋዜጠኞች የሚፈጽሟቸው የሙያ ስነ-ምግባር ጥሰቶች ለምክር ቤቱ የግልግል ዳኝነት ቀርቦ እንዲታይ እንደሚያስችልም አብራርተዋል፡፡ይህም ጋዜጠኞች ያለ ጥፋታቸው እንዳይታሰሩና ካጠፉም በአግባቡ የሚታረሙበት ስርዓት እንዲኖር ከማድረጉም በላይ በመንግስት ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ይቀንሳል ብለዋል።

የግልግል ዳኝነቱ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የሚመራ በመሆኑ ለአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ  በበኩላቸው  መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ተቋም መሆን እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።

“የፖለቲካ ፍላጎት ያለው ሰው ማቋቋም ያለበት የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ ሚዲያ መሆን የለበትም” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጋዜጠኝነት ራሱን የቻለ የተከበረ ሙያ መሆኑን ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።የመገናኛ ብዙሃን ውግንናቸውን ለተቋሙ ባለቤት ሳይሆን ለእውነትና ለህዝብ ማድረግ እንዳለባቸውም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሚዲያ ነጻነትን እንዲከበር እና የጋዜጠኝነት ስነ- ምግባርን አክብሮ የሚሰራ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም እንዲኖር መስራትን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ሲሆን፤ ህጋዊ እውቅና ያገኘውም በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም ነው፡፡

ምንጭENA

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe