(ጥር 24፤2014 ኢቢሲ)የዲሞክራሲ ሂደት እንዲጠናከር የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮዽያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ኢድሪስ አስታውቀዋል፡፡
በተለይም ኢትዮዽያ ውስጥ ላለፉት ጥቂት ወራት የነበረውን የሰላም እጦት ከማረጋጋት አንጻር የውጭ መገናኛ ብዙሃንን የሃሰት መረጃ ከማጋለጥ አንጻር እንዲሁም ነጻና ገለልተኛ ምርጫ በሃገር አቀፍ ደረጃ እንዲካሄድና በአለም ላይ የተጋረጠውን የኮቪድ ወረርሽኝን ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ ከማድረግ አንጻር በኢትዮዽያ ውስጥየሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ትልቅ አስተዋኦ ማበርከታቸውን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙት።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የተናገሩት የኢትዮዽያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት ነው።
የኢትዮዽያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከተመሰረተ ሶስት አመት ተኩል ሆኖታል፤ይሁን እንጂ በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ ደረጃ በነበሩት የኮቪድ ወረርሽኝ እና በሀገር ውስጥ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለመቻሉን ነው በመድረኩ ላይ የተገለጸው።
የኢትዮዽያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከተመሰረተ ከሶስት አመት በላይ ያስቆጠረ እና በአሁኑ ሰዓት የጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን አባላትን ባጠቃላይ 46 የደረሰ ሲሆን፣ በቀጣይ ደግሞ 13 የሚሆኑ አዳዲስ አባላትን እንደሚጨምር ነው በመድረኩ ላይ የተገለጸው።