ጋዜጣዊ መግለጫ
የዓለም የኘሬስ ነፃነት ቀን ዘንደሮ ለ3ዐኛ ጊዜ “መረጃ ለህዝብ ጥቅም” በሚል ርዕስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል፤
(ሚያዝያ 20፤ 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ) የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን የዛሬ 3ዐ ዓመት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በናሚቢያ ዊንድሆክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከበር ሲወሰን መንግስታት ስለኘሬስ ነፃነት እንዲያስቡ እንዲሁም ጋዜጠኞችና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለሙያው ሥነምግባር እንዲተጉ በማሰብ ነው፡፡
የዘንድሮውን የዓለም ዓቀፍ የኘሬስ ነፃነት ቀንም <መረጃ ለህዝብ ጥቅም› <Information as public good> በሚል ዜጐች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የሚያገኙትን ጥቅም በማጉላት የመገናኛ ብዙሃን የኢኮኖሚ አቅም ማረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎች የሚያንፀባረቁበት፣ የኢንተርኔት አቅራቢ ድርጅቶች ግልፅኝነት የሚረጋገጥበት እና ዜጐች የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ትክክለኛነት የሚረዱበትን አቅም በማሳደግ ጋዜጠኝነት እንደ አንድ ዋና መረጃ አቅራቢ በማየት ዋጋ በመስጠት ላይ ያተኩራል፡፡
ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በናሚቢያ ዊንድሆክ የሚከበር ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃም በአዲስ አበባ በዮኒስኮና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በፍሬደሪክ ኤቨርት ስታፍ ቱንግ አስተባባሪነት በስካይላይት ሆቴል ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ወይም May 4/2021 / ይከበራል፡፡
በበዓሉ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፤ምሑራን፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሚገኙ ሲሆን በባለሙያዎች ቀኑን በማስመልከት በተዘጋጁ ጽሁፎች ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡
ቀኑን ስናስብ ዜጐች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት እንዲችሉ መገናኛ ብዙሃን በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ሁኔታ፣ ኮቪድ 19 ያደረሰባቸውን ጉዳት፣ የማህበራዊ ሚዲያው ያለበትን ሁኔታ፣ የጋዜጠኞች ደህንነት በማስጠበቅ ሥራቸውን ከፍርሃት ነፃ ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ትኩረት እንዲያገኝ ለማስቻል ይመክራሉ፤
ስለሆነም የአገራችን መገናኛ ብዙሃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡ ለውጦችን በማጠናከር፣ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ህጐች፣ አሰራሮችና አመለካከት ላይ በመወያየትና ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ ጋዜጠኝነት ይበልጥ ሙያውን ያከበረ፣ ሥነ ምግባሩን የጠበቀ፣ ጋዜጠኞችንም ከስጋት፣ ከፍርሃት ነፃ ሆነው የሚሰሩበትና ዜጐች ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙበትን እሳቤ የሚጐላበት ቀን ሆኖ በአዲስ ስካይላይት ሆቴል ይከበራል፡፡
ዝግጅቱ በኮረና ቫይረስ ስጋት ሳቢያ በአካል ለመገኘት ለማይችሉ በዩኔስኮ ድረ ገፅ የቀጥታ ስርጭት ስለሚኖረው ፕሮግራሙን መከታታል የሚችሉ ሲሆን ተሳትፎ ለማድረግ ለሚፈልጉ ወገኖች የዊበናር ምዝገባ እንዲያደረትጉ ይመከራል፡፡