የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ሚያዚያ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ባዘጋጀው የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር ማኅበሩን በመመስረት እና የስራ አስፈፃሚ አባል በመሆን ያገለገሉ ጋዜጠኞችን እና ማኅበሩን በተለያየ መንገድ ለደገፉ አጋዥ የምስጋና እና ምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡ የምስጋና መርሃ ግብሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ሚድያ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ታምራት ሀይሉ ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
ማኅበሩን በመመስረትና የሥራ አስፈፃሚ አባል በመሆን የተመሰገኑትና እውቅና የተሰጣቸው የማኅበሩ የመጀመሪያ ፕሬዚዴንት የነበረው ጋዜጠኛ ኤሌያስ መሰረት፣ ጋዜጠኛ ኤርሚያስ በጋሻው፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ሐብታሙ ደባሱና ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ማኅበሩን በአጋርነት በማገዛቸው ከተመሰገኑት አጋር አካላት መካከል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ዴክሲስ ኮንሱልታንሲ ግሩፕ፣ ራይድ ( ሀይብሪድ ዲዛይንስ ፒኤልሲ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ዩኔስኮ፣ ቤስት ዌስተርን ፕላስ ፔርል አዲስ ሆቴል፣ ቴክኖ ብሮስ፣ አፍሪኮም ቴክኖሎጅስና ዳጉ ኮምንኬሽን ፒኤልሲ ይገኙበታል፡፡
ማኅበሩ ከተመሰረት አጭር ጊዜ ቢሆንም እስካሁን በነበሩት ጊዜያት ለጋዜጠኞች መብት በመቆርቆር፣ ለዘርፉ ባለሙዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ ወርሃዊ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ዳሰሳ በመሥራት፣ በዘርፉ ላይ የሕግ ጥሰቶች ሲያጋጥሙና የውጭ ሚዲያዎች የተሳሳቱ መረጃዎችን ስለ ኢትዮጵያ ሲዘግቡ እንድታረሙ በማድረግ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ በእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት አጋር አካላትና የመንግሥት ኃላፊዎች በቀጣይ ማኅበሩን እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል፡፡