ዜናየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት ከ2 ዓመት በኋላ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት ከ2 ዓመት በኋላ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

 የግልግል ዳኝነት አካል የአሰራር ደንብ አጽድቋል

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት ባለፈው ማክሰኞ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ከሁለት ዓመት በኋላ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን በዕለቱም የግልግል ዳኝነት አካል የአሰራር ደንብን አጽድቋል። በ2012 እና በ2013 ዓ.ም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የም/ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤዎች ሳይከናወኑ መቅረታቸው ተጠቁሟል።
የምክር ቤቱን የሁለት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የም/ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ፣ ም/ቤቱ በአገሪቱ መሰረታዊ የሆኑት የሕግ የበላይነትና የፕሬስ ነጻነት እንዲከበሩ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፤
ም/ቤቱ ባካሄደው በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያለፉት ሁለት ዓመታት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የግልግል ዳኝነት አካል የአሰራር ደንብንም አጽድቋል።
ም/ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፈረንሳይ መንግስትና ከዩኔስኮ በተገኙ ድጋፎች፤ የአቅም ግንባታ፣ ጽ/ቤት የማደራጀት እንዲሁም የግልግል ዳኝነት የማቋቋም ሥራዎችን ማከናወኑ ተገልጿል።

Participants
Participants

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ኢድሪስ፤ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ጠንካራ ሚናውን በአግባቡ የሚወጣ መገናኛ ብዙኃን ሲኖር፣ ሚናውን በአግባቡ የሚወጣ ህዝብና መንግስት ይኖራል” ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃን፤ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት ህዝቡን በማንቃት፣ ምርጫ 2013 በሰላም እንዲጠናቀቅ እንዲሁም አገሪቱ ባጋጠማት የህልውና ፈተና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በማጋለጥ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱን የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ያቀረቡት የም/ቤቱ ጽህፈት ቤት አባል አቶ ታምራት ኃይሉ፤ የአባላትን ቁጥር ማሳደግ፣ የፕሮጀክት ስራዎች፣ ስልጠናና የገቢ ማስገኛ ሥራዎች፣ የዘገባ ማኑዋል ማዘጋጀት፣ የአባላት መዋጮን ማስፋት፣ የሚዲያ መከታተያ (ሞኒተሪንግ) ክፍል ማደራጀት እንዲሁም የግልግል ዳኝነትና የዕንባ ጠባቂ አካል ማደራጀት በዕቅዱ ውስጥ መካተታቸውን ጠቁመዋል።
በ19 መስራች አባላት  የተመሰረተው ም/ቤቱ፤ በዕለቱ ጉባኤ ላይ የአባልነት ጥያቄያቸው የፀደቀላቸውን 13 የመገናኛ ብዙኃንና የሙያ ማህበራትን ጨምሮ በአጠቃላይ የአባላቱ ቁጥር 60 መድረሱ ታውቋል። እንዲያም ሆኖ ሁሉም የም/ቤቱ አባላት የአባልነት መዋጮ በአግባቡ እየከፈሉ ባለመሆኑ ም/ቤቱ በፋይንስ እጥረት እንደሚቸገር ተነግሯል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት የራሱን ባለ 7 ክፍሎች ጽ/ቤት ማደራጀቱንና ራሱን የሚያስተዋውቅበት ድረ-ገጽ መጀመሩን በዕለቱ ይፋ አድርጓል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe