ዜናየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የግልግል ዳኝነት አካል የአሠራር ደንብ አፀደቀ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የግልግል ዳኝነት አካል የአሠራር ደንብ አፀደቀ

  • ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዶ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርቧል

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ማክሰኞ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢንተር ላግዠሪ (የቀድሞው ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል) ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ የግልግል ዳኝነት አካል ደንብ አፀደቀ፡፡

ይኼ የግልግል ዳኝነትና የዕንባ ጠባቂ አካል በምክር ቤቱ የ2014 ዓ.ም. ዕቅድ ውስጥ የተካተተ ሲሆን፣ 18 የግልግል አካሉ አባላትም ተመርጠው ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ከጠቅላላ ጉባዔ አባላት ጋር መተዋወቃቸው በምክር ቤቱ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በ2012 ዓ.ም. እና በ2013 ዓ.ም. መከናወን የነበረባቸው ጠቅላላ ጉባዔዎች ሳይከናወኑ መቅረታቸውን በመግለጽ፣ የምክር ቤቱን የሁለት ዓመታት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ፣ ምክር ቤቱ በአገሪቱ መሠረታዊ የሆኑት የሕግ የበላይነትና የፕሬስ ነፃነት እንዲከበሩ በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ-መገናኛ-ብዙኃን-ምክር-ቤት-የግልግል-ዳኝነት-አካል
የኢትዮጵያ-መገናኛ-ብዙኃን-ምክር-ቤት-የግልግል-ዳኝነት-አካል

ምክር ቤቱ እስካሁን 46 አባላት የነበሩት ቢሆንም፣ በጥር 24 ቀን ጉባዔ ላይ አባልነት የጠየቁ 13 የመገናኛ ብዙኃንና የሙያ ማኅበሮች ጥያቄያቸው ተቀባይነት በማግኘቱ የአባላት ቁጥር ወደ 60 አድጓል፡፡

ከዚህ ባለፈ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምክር ቤቱ ከፈረንሣይ መንግሥትና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በተገኙ ድጋፎች ለአቅም ግንባታ ሥራዎች፣ ለቢሮ ማደራጀት፣ ለግልግል ዳኝነት፣ እንዲሁም ለአምስት ዓመታት ስትራቴጂ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢው አቶ አማረ አስረድተዋል፡፡

የግልግል ዳኝነት አካል ደንብና የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ከፍተኛ በአማካሪዎች የተዘጋጀ መሆኑን፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በተደረገም ምክክር የመገናኛ ብዙኃንን የተመለከቱ ጉዳዮች በምክር ቤቱ ግልግል ዳኝነት እንዲስተናገዱ ለማድረግ ከስምምነት መደረሱም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ በማስታወቂያ ምክንያት የቀረቡባቸው ክሶችን በተመለከተ ቅሬታ ስለነበር፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ጋር ውይይት መደረጉ ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ እየተዘጉና ደመወዝ መክፈል ተስኗቸው የነበሩ የሚዲያ ተቋማት እንደነበሩ፣ እንደ ሆቴል ላሉ ዘርፎች እንደተደረጉ ድጋፎች ለመገናኛ ብዙኃንም የብድር አቅርቦትና የታክስ ዕፎይታ እንዲደረግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ጥያቄ ቀርቧል ሲሉ አቶ አማረ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የምክር ቤቱ ሥራዎችን ካስተጓጎሉ ጉዳዮች አንዱ፣ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት የአባላት መዋጮ በአግባቡ እየከፈሉ አለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ምክንያት የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ሥራዎች በጥቂት አባላት መዋጮ ብቻ እየተከናወኑ ነው ተብሏል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት መዋጮን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ በአባላት ላይ አስገዳጅ የሆነ አሠራር ቢኖር ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የጠቅላላ ጉባዔው ሰብሳቢ ወ/ሮ ትዕግሥት ይልማ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ምክር ቤቱን የማስተዋወቅ ዝግጅቶችን ጨምሮ ከጋዜጠኞች ጋር በግጭት አፈታትና በሰላም ጋዜጠኝነት ላይ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ መገናኛ ብዙኃን ምርጫ 2013 ዓ.ም. ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፣ እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝን የተመለከቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራትና በቅርቡም አገሪቱ ገጥሟት በነበረው ፈተና ሚዲያው የተወጣው ሚና በማውሳት አድንቀዋል፡፡

ሆኖም ከሙያ ሥነ ምግባር ማፈንገጥና በግል ፍላጎት ጥቅሞች መጠለፍ የመሳሰሉ የሚዲያ ተግዳሮቶች መታየታቸውንና በሚዲያው የፖለቲካ ፍላጎት፣ የማኅበረሰብ አንቂነትና የጋዜጠኝነት መደበላለቅ ይታያል ሲሉ ተችተዋል፡፡

የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አባል አቶ ታምራት ኃይሉ የምክር ቤቱን የ2014 ዓ.ም. ዕቅድ ሲያቀርቡ አባላትን ማሳደግ፣ የፕሮጀክት ሥራዎች፣ ሥልጠናና የገቢ ማስገኛ ሥራዎች፣ የዘገባ ማኑዋል ማዘጋጀት፣ የአባላት መዋጮን ማስፋት፣ ስለምክር ቤቱ የተዛቡ አመለካከቶችን ማስተካከል፣ የሚዲያ መከታተያ (ሞኒተሪንግ) ክፍል ማደራጀት፣ እንዲሁም የግልግል ዳኝነትና የዕንባ ጠባቂ አካል ማደራጀት በዕቅዱ ውስጥ መካተቱን አስታውቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ይሠራሉ ተብለው የተቀመጡ ሥራዎችን ለማከናወን በአጠቃላይ 1.638 ሚሊዮን ብር በጀት የሚጠይቅ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 941543 ብር ከአይኤምኤስ የፕሮጀክት ድጋፍ የተገኘ ነው ብለዋል፡፡

በቀረበው በጀትና ዕቅድ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላም ጠቅላላ ጉባዔው አፅድቆታል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ አስፈጻሚ አባልነት በለቀቁ ሁለት አባላት ምትክ ማለትም በሔኖክ ሥዩም (ዶ/ር) ምትክ አቶ ንጉሤ መሸሻና በጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ምትክ አቶ አማን ፍስሐጽዮን ተመርጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገኛኛ ብዙኃን ምክር ቤት የራሱ ጽሐፈት ቤት ያለው፣ ኢንተርኔትና ድረገጽ በማሟላት፣ የግልግል ዳኝነት ሥራውንም ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁንና ሥራውን በተጠናከረ ሁኔታ እየሠራ መሆኑን በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተገልጿል፡፡ 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe