ዜናየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄደ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄደ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በሌግዥሪ ሆቴል ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄደ፡፡ በጉባዔው ላይ የምክር ቤቱን የግልግል ዳኝነት አካል የአሰራር ደንብ አፀደቀ፡፡ የምክር ቤቱን የመተዳደሪያ ደንቡን አሻሻለ፡፡

በዚሁ ጉባዔ ላይ የምክር ቤቱ ሙሉና እጩ አባላት፣ የስራ አስፈፃሚ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ ወ/ሮ ትዕግስት ይልማ በቅድሚያ የጠቅላላ የጉባኤውን አባላትና ተሳታፊዎች ጥሪውን አክብረው በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፣ ምክር ቤቱ ሰኔ 2011 ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ ስራ መጀመሩ፣ ከተለያዩ አገራት የሚዲያ ምክር ቤቶችን በመቀመርና ለስራው መጀመር የሚበጁ የተለያየ የመሰረት ድንጋዮችን በማስቀመጥ ረገድ በተለይ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የተለያዩ ጥረቶች ሲደርግ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

Wro Tigest Yilma , head of general assembly
Wro Tigest Yilma , head of general assembly

እንዲሁም ባለፉት ሁለት አመታት ገደማ ምንም እንኳን ኮቪድ 19ኝን የመሰሉ ዓለም አቀፍ ጫናዎች በምክር ቤቱ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅህኖ ያሳደሩ ቢሆንም፣ የተለያዩ አቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለማህበሩ አባል ተቋማት ሙያተኞች መስጠቱና እንደ ምርጫ 2013ን የመሰሉ አገራዊ ተልእኮዎችን በሚያግዝ መንገድ ጋዜጠኞችን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት ማድረጉን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በተቀረፁት ፕሮጀክቶች መሰረት የፈረንሳይ መንግስትን የመሰሉ አጋር አካላት ለፕሬስ ነፃነትና ለዲሞክራሲ ማበብ በሚረዳ መንገድ ድጋፍ ማድረጋቸውን፣ ይሁንና በምክር ቤቱ ህገ ደንብ መሰረት አባል ተቋማትና ማህበራት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በማዋጣት በኩል ጉድለት እንደነበረባቸው አስታውቀዋል፡፡ በመጨረሻም ለምክር ቤቱ ድጋፍ ለአደረጉ አካላትና አጋሮች ሁሉ ምስጋና በማቅረብ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ባደረጉት ንግግር በአገራችን  የህዝብ እድገትና ብልፅግና ለማረጋጋጥ፣ አገር ሰላምና ደህንነትን እውን ለማድረግ፣ ብሎም የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና ሉአላዊነት ለማስፍን መገናኛ ብዙሃን የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑንና አገራችን የጀመረችውን ለውጥ ለማጠናከር እንዲሁም በዲሞክራሲው ስነምህዳር የዜጎች ተሳትፎ እንዲጎለብት፣ በተለይም ባለፈው አመት በተካሄደው ምርጫና በስልጣን ርክክብ ወቅት መገናኛ  ብዙሃንና ሙያተኞቹ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

Ato Mohamed Eders, Director of EMA
Ato Mohamed Eders, Director of EMA

ይሁንና በአገራችን ጋዜጠኝነት፣ የማህበረሰብ አንቂነትና የፖለቲካ ታዋናይነት እየተቀላቀሉ በመምጣታቸው ለመገናኛ ብዙሃን ነፃነት፣ ሚዛናዊነትና ገለልተኝነት እንቅፋት እየሆነ መምጣቱ፣ ለዚህ ደግሞ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በተለይም የማህበራዊ ድረገፅ አጣቃቀም ማደጉ አንዳንድ ግለሰቦች የሃሰት መረጃና ያልተጨበጡ ጉዳዮችን ጭምር በመልቀቅ ለዲሞክራሲው ማበብ ፈተና መሆናቸው ዋናው ዳይሬክተር አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም በእኛም አገር የስም ማጥፋት፣  የጥላቻ ንግግሮች የተሳሳተ መረጃ መብዛት የፕሬስና መገናኛ ብዙሃን መስኩን ክፉኛ እያወኩ እንደመሆናቸው፣ በመንግስት ተቆጣጣሪ አካላት ብቻ ሳይሆን ሙያተኞችና ራሳቸው የሚዲያ ተቋማቱ በሚያቋቁሟቸው ይህን ምክር ቤት በመሰሉ አካላት እያረሙ መሄድ የግድ አስፈላጊ መሆኑን አቶ መሐመድ እድሪስ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ መንግስት የዚህን ምክር ቤት መጠናከር እንደሚፈልግና የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪው ሙያዊ ጥረት እንዲጎለብትም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ፣ በምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ፣ በአባላቱና የግልግል ዳንኝነት ስራን በሚሰሩ ወገኖች በኩልም ይህንኑ በመገንዘብ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስታውሰዋል፡፡

በመቀጠልም የፈረንሳይ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ሚስተር ክላውድ ቢሊቪን ባሰሙት ንግግር እንደገለፁት ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከአንድ ምእተ አመት ለሚልቅ እድሜ ከገነቡት የሁለትዮሽ ወዳጅነት አንፃርም፣ የአገራቸው መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መረጋጋት፣ እድገትና ዲሞክራስያዊነት አስፈላጊ ድገፋና እገዛ ከማድረግ እንደማይቆጠብ ተናግረው እንደ ሲቪክ ማህበር ለዚሁ ምክር ቤት እያደረገ ያለው ድጋፍና እገዛም ከዚሁ ሁሉ አቀፍ ትብብር ተነጥሎ እንደማይታይ አስረድተዋል፡፡

Mr Cloud Bevilin, French ambassador representative
Mr Cloud Bevilin, French ambassador representative

ለፕሬስ መጎልብት፣ ለአመለካካትና የሀሳብ ነፃነት መንግስት ያወጣቸውን ህግጋት በአግባቡ እንዲተገበሩ ማድረግ እዳለበትና የፕሬስ ነፃነት ዋነኞቹ ባለቤቶች የሆኑት ባለሙያዎችና የሚዲያ ተቋማትም  በሃላፊነት ስሜት፣ በታማኝነትና በእውነት ላይ ተመስርተው ተግባራቸውን ማከናዎን እንዳለባቸው ለዚሀ ደግሞ በሙያ ስነምግባርና መርዕ መመራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በብዙ ታዳጊ አገሮች የፕሬሱም ሆነ የአገር መረጋጋት ፈተና እየሆኑ ያሉ የጥላቻ ንግግሮችን ማረም እደሚገባ፣ ለዚህ ደግሞ የምክር ቤቱ መመስረት ብቻ ሳይሆን መጠናከርና ወደስራ መግባት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ገልፀው በቀጣይ የፈረንሳይ ኤምባሲ ድጋፍና አጋርነቱ እንደማይለይ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ዓመታዊ ሪፖርት ያቀረቡት የስራ አስፈፃሚው ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ እንደተናገሩት የምክር ቤቱ ስራ በተቀላጠፈ መንገድ እንዲከናወን ለማስቻል የመጀመሪያ ተግባር የነበረው ፅ/ቤቱን በሰው ኀይልና በቁሳቁስ ማሟላት ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት የጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ፣ የፕሮጀክትና የፋይናንስ ባለሙያዎች ቅጥር ፈፅሟል፡፡ እንዲሁም ለፅህፈት ቤቱ እና ለእንባ ጠባቂና ለይግባኝ ሰሚ የዳኝነት አካሉ የሚሆኑ የቢሮ ቁሳቁሶች ማለትም ጠረጴዛና ወንበር፣ ኮምፒውተሮች፣ ፕሪንተሮች ግዢዎች ተከናውኗል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የምክር ቤቱን ድረ ገፅ ወይም ዌብ  ሳይት በአማርኛና በእንግሊዝኛ አሰርቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡  ጽህፈት ቤቱን ለማጠናከርና ምክር ቤቱ የራሱን ቋሚ ቢሮ ስላልነበረው በግለሰብ ህንጻ ላይ ለአንድ ክፍል ከፍተኛ ኪራይ በመክፈል ነበር ስራውን ሲያከናውን የነበረው፤ ሆኖም ይህን ወጪ ለመቀነስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ወደ መንግስት ቤቶች ኤጀንሲና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ደብዳቤዎችን በመፃፍና በተደጋጋሚ በአካል በመሄድ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት መስቀል አደባባይ በሚገኘው ፊንፊኔ ህንፃ ላይ ባለ 7 ክፍል ቢሮ ከመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ በኪራይ ተረክቦ ስራውን እያከናወነ  መሆኑን ገልፀዋል፡፡

Ato Amare Aregawi, head of Executive Committee
Ato Amare Aregawi, head of Executive Committee

ሰብሳቢው በመቀጠልም ባለፈው በጀት ዓመት 2013 የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ሳይቻል ቀርቷል፤ ስብሰባውን ለማካሄድ ያልተቻለው በዋናነት በኮቪድ 19 ምክንያት በርከት ያሉ ሰዎችን የያዘ ስብሰባ ለማካሄድ በጤና ሚኒስቴር በኩል በወጣው የኮቪድ ፕሮቶኮል መመሪያ ምክንያት ሲሆን ሌላው ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪን ለመሸፈን በፅ/ቤቱ በኩል አዳጋች በመሆኑ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን በጽ/ቤቱ በኩል ለስብሰባው የሚያስፈልገው የእቅድ ዝግጅትና በጀት ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ እንደማይቻል ተጠቅሶ ለአባላት በየቢሮአቸው በተላከ ደብዳቤ እንዲያውቁት መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አማረ አረጋዊ በመቀጠልም የምክር ቤቱን የግልግል ዳኝነት አካል ማቋቋምን በተመለከተ ም/ቤታችን የተቋቋመበትን አብይ አላማ ለማከናወን ዋናውን ሚና የሚጫወተው ይህ የግልግል ዳኝነት አካሉ እንደመሆኑ መጠን ህገ ደንባችን በሚፈቅደው ድንጋጌ መሠረት 18 አባላት ያሉት የግልግል የዳኝነት አካል መቋቋሙን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የፕሮጀክት ስራዎችን በተመለከተ አቶ አማረ አረጋዊ እንዳስረዱት ከፈረንሳይ ኤምባሲ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ማለትም 4,347,826.09 (አራት ሚሊየን ሦስት መቶ አርባ ሰባት ሺህ ስምንት መቶ ሃያ ስድስት ብር 09/100 ብር) የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ባለፈው ዓመት በአገራችን የተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ በማድረግ በኩል የጋዜጠኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ይህንኑ መሰረት በማድረግም በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ጋዜጠኞች ስልጠና መሰጠቱትንና የስልጠናው ትኩረትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫ ዘገባ የስነ ምግባር ደንብ እና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አደረጃጀትና አሰራር ዙሪያ ላይ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ቤትና ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በመጡ ባለሙያዎች ለአዲስ አበባ፣ ለአማራ ክልል፣ ለኦሮሚያ፣ ለደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ለሲዳማ ክልል፣ ለድሬደዋ፣ ለሶማሌና ለሐረሪ ክልል በድምሩ ለ219 ጋዜጠኞች በየክልላቸው በመገኘት ስልጠና መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡

ሌላው በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ በባለሙያ እንዲዘጋጅ ከግልግል አካሉ ጋር በተደረገ ስምምነት ህጋዊ የጋዜጣ ማስታወቂያ ወጥቶ ሞሽን ኮንሰልታንሲ የተባለ ድርጅት አሸንፎ በጽ/ቤቱ ድጋፍ ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

Head of Arbitration commission
Head of Arbitration commission

በመጨረሻም በ19 መስራች አባላት የተመሠረተው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት እስከ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ የአባላት ቁጥር ወደ 45 ከፍ ማለቱንና  ከዚያ ወዲህ በምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ አባላት ያላሰለሰ ጥረትና ጉትጎታ የአባልነት መስፈርቱን አሟልተው በመመዝገብ የዛሬውን የጠቅላላ ጉባዔችንን ውሳኔ የሚጠባበቁ-14 እጩ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶችና የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራት መገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የምክር ቤቱ የኦዲት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በቀረበውም ዓመታዊ ሪፖርትና ዕቅድ እንዲሁም የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ የቀረበ ሲሆን የግልግል ዳኝነቱ ረቂቅ ደንብ አሰራርን በተመለከተ በግልግል ዳኝነት አመራሮች አቶ ፊሊጶስ አይናለም እና በዶ/ር ንጉሴ ተፈራ ማብራሪያ ቀርቦ ውይይትና አስተያየት ቀርቦ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡

With Elected leaders
With Elected leaders

የአባልነት ጠያቄ ያቀረቡ 14 አባላትን በሙሉ ድምፅ በመቀበል የአባላት ቁጥር ወደ 60 ያደገ ሲሆን ከምክር ቤቱ በተጓደሉ አመራሮች ምትክ ምርጫ ተካሂዶ ለምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ም/ሰብሳቢ ንጉሴ መሸሺያ (ዶ/ር) ከዋልታ ለስራ አስፈፃሚነት ደግሞ አቶ አማን ፍሰሃጽዮን (ከኢ.ቢ.ኤስ) ተመርጠዋል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe