ዜናየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አመራሮች ከኡጋንዳ ሚዲያ ካውንስል ጋር የልምድ ልውውጥ...

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አመራሮች ከኡጋንዳ ሚዲያ ካውንስል ጋር የልምድ ልውውጥ አደረገ

የኡጋንዳ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት ባደረገለት ግብዣ 5 አባላትን የያዘ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት የልዑካን ቡድን ከየካቲት 20 – 24/2014 ዓ.ም. ወደ ኡጋንዳ አቅንቶ የልምድ ልውውጥ አደረገ፡፡

President of Media council of Uganda
President of Media council of Uganda

የመገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ራሳቸውን በራሳቸው ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን የግልግል ዳኝነት የአሰራር ስርአት የዘረጋው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት በጅማሮ ላይ ለሚገኘው እንቅስቃሴው ተሞክሮ ለመቅሰም ነበር ወደ ኡጋንዳ – ካምፓላ ያቀናው፡፡

የኡጋንዳ የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤት የአመራር አካላት ለልኡካን ቡድኑ አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት ለልምድ ልውውጥ ኡጋንዳን በመምረጡ አመስግነዋል፡፡

በማርዮት ኢንተርናሽናል የፕሮቲ ሆቴሎች አዳራሽ በተዘጋጀ የትውውቅ ፕሮግራም ላይ የኡጋንዳው የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤት አመራር አካላት ለኢትዮጵያ አቻቸው ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት ስለ ም/ቤታቸው አደረጃጀት፣ ስለተቋቋመበት ዓላማና ተግባር፣ ስለ ግጭት አፈታት፣ ስለ አጋጠሙት ፈተናዎችና ስለ መልካም እድሎቹ … ስለሚመሩበት የጋዜጠኞች የሙያ ስነምግባር ድንጋጌዎች፣ በሰፊው ገለፃ  ያደረጉት የኡጋንዳ ሚዲያ ካውንስል ፕሬዚዳንት ሚስተር ፖውል ፓውሎ ኢኮቹ ምክር ቤቱ በአዋጅ የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው መንግስት በስራው ጣልቃ እንደማይገባና የአሰራር ነፃነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃንን በሙሉ ፈቃድ በመጠትና በመቆጣጠር ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያው ልኡካን በኩልም ስለ ም/ቤቱ የአደረጃጀት ባህርይና ጅምር እንቅስቃሴው ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ምክር ቤቱ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ ስራ ከጀመረ ገና ሶስት ዓመት ቢሆነውም በመገናኛ ብዙሃን ላይ በሚቀርቡ ዘገባዎች ዙሪያ ከህዝብ ከመንግስትና ከሚዲያዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ተቀብሎ የሚመረምር የግልግል ዳኝነት አካል አዋቅሮ ስራ ለመጀመር በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገለፃ ተደርጓል፡፡ አጥጋቢ ውይይትም ተካሂዷል፡፡

EMC delegation
EMC delegation

እ.ኤ.አ. በ1995  በመንግስት አዋጅ የተቋቋመው የኡጋንዳ የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤት የመንቀሳቀሻ በጀት የሚመደብለት በመንግስት ሲሆን የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤት ደግሞ በሙያተኞች በፈቃደኝነት የተቋቋመና የባጀት ምንጩም ከአባላቱ መዋጮና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች የሚገኝ  መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤት የልኡካን ቡድን በ4 ቀናት የካምፓላ ቆይታው ፕራይም ቴሌቪዥንን ፤ ዩጋንዳ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን፤ ኒው  ቪዥን ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልንና የማካራሬ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል እንዲሁም የኡጋንዳ ብሄራዊ ሙዚየምን ጐብኝቷል፡፡ በአገሪቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና ናሽናል ጋይዳንስ ሚኒስቴር በመገኘትም ከሚኒስትሯ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡

Visiting in Vision Group
Visiting in Vision Group

በኡጋንዳ የኤፌዴሪ አምባሳደር ክብርት ወ/ሮ አለምፀሐይ መሠረት በተገኙበት በዚህ መድረክ ምክትል ሚኒስትሯ ዶ/ር ክሪስ ባርዮሙንሲ የኢትዮጵያ የሚዲያ ካውንስል ለልምድ ልውውጥ ወደ ኡጋንዳ መምጣቱ ትክክለኛ ምርጫ በመሆኑ አክብሮታቸውን ገልፀዋል፡፡ አክለውም ሁለቱን አገሮች በሚዲያው ነፃነት ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው የሚያሳይ መልካም ጅማሮ ነውና ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደግፋለን ብለዋል፡፡

State minster of ICT
State minster of ICT

በኡጋንዳ የኢፌዴሪ አምባሳደር ክብርት ወ/ሮ አለምፀሐይ መሠረት በበኩላቸው የሁለት እህትማማች አገሮች የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤቶች ያደረጉት የልምድ ልውውጥ ነፃ እና ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ ለመገንባት ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር ኢትዮጵያ ለጀመረችው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ዋጋ ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ የታላቁ የናይል ወንዝ ዋነኛ አካሎች የሆኑት የጥቁር አባይና የነጭ አባይ መፍለቂያዎች መሆናቸውን ያወሱት አምባሳደር አለምፀሐይ መሠረት ሁለቱ አገሮችን የሚያስተሳስሩ መልከአ ምድራዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እንዲሁም የፓን አፍሪካዊነት ፖለቲካዊ እሴቶች ያሏቸው እህትማማች አገሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እናም ይህን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሁለቱ አገሮች የሚዲያ ባለሙያዎችና ምክር ቤቶቻቸው ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤት የልዑካን ቡድን በካምፓላ ቆይታው ጠቃሚ ተመክሮ ያገኘ መሆኑንና ለጉብኝቱ መሳካትም የኡጋንዳ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት እና በኡጋንዳ የኢፌዴሪ ኢምባሲ በተለይም ክብርት አምባሳደር አለምፀሐይ መሠረትና ባልደረቦቻቸው ላደረጉት ከፍተኛ ትብብርና ድጋፍ ምስጋናውን ገልፃል፡፡

Ethiopia Ambassador with EMC delegation
Ethiopia Ambassador with EMC delegation

በመጨረሻም ለልኡካን ቡድኑ መሰነባበቻ በታዋቂው የንድሬ የባህል ማዕከል አስደሳች ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት የቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤት የልኡካን ቡድን የኡጋንዳ አቻውን ለተመሳሳይ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ጋብዟል፡፡

Uganda traditional music
Uganda traditional music

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe