ሶስት አባላትን ያከተተው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አመራሮች በሩዋንዳ ሚዲያ ኮሚሽን ጋባዥነት ከሚያዝያ 17 እስከ 21 ቀን 2014 ዓም ድረስ በሩዋንዳ ኪጋሊ ተገኝተው የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡
በልምድ ልውውጡ ላይ የተሳተፉ የምክር ቤቱ አመራሮች አቶ ታምራት ኃይሉ (የምክር ቤቱ የስራ አስፈፀሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ)፤ዶ/ር ንጉሴ መሸሻ (የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ም/ሰብሳቢ) እና ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ (የምክር ቤቱ የግልግል ዳኝነት አባል) ሲሆኑ በቆይታቸው የሩዋንዳ የመገናኛ ብዙሃን ኮሚሽን ቢሮንና የሩዋንዳ ዩቲሊቲ ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ፣ የተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎችን፣ የሩዋንዳ ዩቲሊቲ ተቆጣጣሪ ባለስልጣንና በመጨረሻም የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋን መታሰቢያ ሙዚየም ተመልክተዋል፤
የሩዋንዳ መገናኛ ብዙሃን ኮሚሽን የተመሰረተው በ2013 እ.ኤ.አ ሲሆን የህግ ሰውነት ያገኘው በአዋጅ ነው፡፡ መንግስታዊ ተቋም ተደርጎ የተቋቋመው የሩዋንዳ ሚዲያ ኮሚሽን በመንግስት ለጋዜጠኞችና ለኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ኮሚሽኑን በበጀት ይደግፋል፡፡ የጽህፈት ቤት ህንጻ አበርክቷል፡፡ ቦርዱ ከመንግስት የበጀትና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ማግኘቱ ነጸነቱን ሳይጋፋው የኢኮኖሚ ጉዳይ ሳያሳስበው ስራውን እንዲቀጥል እየረዳው መሆኑን ተገልፃል፡፡
የኮሚሽኑ ዋነኛ ተግባራት፣ የሚዲያውን ይዘት መቆጣጠር፣ እናም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችንና ተቋማት መመዝገብና የሙያተኝነት እውቅና መስጠት (accreditation)፣ የምክርና የግንዛቤ ማስጨበጥ አገልግሎት፣ ውይይቶችንና አውደጥናቶቾን ማዘጋጀት፣ እና የመገናኛ ብዙሃንና ህብረተሰብ ግንኙነትን አስመልክቶ ያሉ ህግና ስርዓቶችን ማስተዋወቅ ወይም ግንዛቤ መፍጠር ናቸው፡፡
የኮሚሽኑ ተልእኮ፣ ነጻ፣ ራሱን ችሎ የሚተዳደርና ተጠያቂነት ያለበት መገናኛ ብዙሃንን መፍጠርና ማበረታታት ሲሆን በዚህም መሰረት ከሙያ ስነምግባርና ከጋዜጠኝት መርህ ወጣ ያሉ ጋዜጠኞችንና የመገናኛ ብዙሃንን ተቋማት በ2014 እ.ኤ.አ ተሻሽሎ በጸደቀው የስነምግባር መተዳደሪያ ደምብ መሰረት እርምጃ ይወስዳል፡፡የስነምግባር መመሪያው በሶስት ቋንቋዎች ማለትም በኢኒኪንያሩዋንዳ፣ በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ የተዘጋጀ ሲሆን 34 አንቀጾች አሉት፡፡
ሩዋንዳ የሚዲያ ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ፣ 466 ያህል ቅሬታዎችን ከህዝብና ከተቋማት ተቀብሏል፡፡ ዋናዋናዎቹ የቅሬታ ምንጮች፣ የሌላን ሰው ወይም መገናኛ ብዙሃን ስራ የራስ አድርጎ ማቅረብ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘቶች ሳያጣሩ መዘገብና የስም ማጥፋት ዘገባዎች ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ 24 ሰዓታት የሚዲያ ይዘቶችን ይቀዳል፡፡ ለ6 ወራት ያህል የሚያስቀምጥበት የመረጃ ቋት አለው፡፡ ስድስት ወራት የሞላቸውን ይዘቶች ፈላጊ ወይም ቅሬታ አቅራቢ የላቸውም ተብሎ ስለሚታሰብ ይሰርዝና ማሽኑን ለቀጣይ ዘገባ ይጠቀምበታል፡፡ ቅሬታ ቀርቦባቸው የነበሩትን ይዘቶች ደግሞ ለሰነድነት ያስቀምጣል፡፡
በሩዋንዳ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤት ለመሆን የግድ ሩዋንዳዊ መሆን ግድ አይደለም፤ ከሩዋንዳውያን ውጪ ላሉም ዜጎች ሚዲያ መክፈት ይችላሉ፡፡ኮሚሽኑ የሙያተኛነት ፈቃድ የሚሰጣቸው፣ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ የውጭ አገር ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት (ህትመትና ኦንላይን) ናቸው፡፡ ይህንን የኮሚሽኑን ፈቃድ ካርድ ልያዘ ማንኛውም ጋዜጠኛ በስራ ላይ መሰማራት አይችልም፤ስራ ሲለቅም የፕሬስ ካርዱን ለኮሚሽኑ ይመልሳል፤
በኮሚሽኑ 205 የሚሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሲመዘገቡ 969 ጋዜጠኞች (743 ወንዶችና 226 ሴቶች) ከኮሚሽኑ የስራ ብቃት ማረጋገጫ ወይም አክሬዲቴሽን ወስደዋል፡፡ ዘጠኝ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችና 196 ህትመትና ኦንላይን ሚዲያ ተቋማት ተመዝግበዋል፡፡
አንድ ጋዜጠኛ ከሚሰራበት የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ሲለቅ፣ የተሰጠውን ፈቃድ ይመልሳል፡፡ ምክንያቱም ለፈቃድ ሲያመለክት የሚሰራበት ተቋም ይሁንታ አብሮ ስለሚያቀርብ ማለት ነው፡፡
ቡድኑ ሌላው የተመለከተው የኬንያሩዋንዳ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘውን የሮያል ኤፍ ኤም 94.3 ሬዲዮ ጣቢያ ጉብኝት ሲሆን፣ጣቢያው የሚተዳደረው በማውንት ኬንያ ዩኒቨርሲቲ ነው፤ ጣቢያው በ2013 እ.ኤ.አ ሲቋቋም በስሩ ለተከፈተው የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት ተማሪዎች ተግባራዊ ትምህርትና ልምምድ ተብሎ የተቋቋመ ነው፡፡ ከተማሪዎች መለማመጃነቱም ባሻገር የዩኒቨርሲቲው ልሳን በመሆን ያገለግላል ፡፡ ጣቢያው የአገልግሎቱን 40 በመቶውን ሽፋን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሆኖ 60 በመቶው ሽፋን ደግሞ የሩዋንዳ ቋንቋ በሆነው በኢኪንያሩዋንዳ (Ikinyarwanda) ነው፡፡ በየቀኑ የ14 ሰዓት ስርጭት አለው፡
ሌላው ቡድኑ የጎበኘው በወጣት ባለሃብቶች የተመሰረተውን ኪጋሊ ቱዳይ የተሰኘውም መልቲ ሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ኪጋሊ ቱዳይ የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ2011 ነው፡፡ ኪጋሊ ቱዴይ በአገሪቱ ካሉት የግል ጣቢያዎች ትልቁ ነው፡፡ ጣቢያው በኮቪድ ምክንያት ከህትመት ውጪ የሆነውን ጋዜጣ ጨምሮ፣ ባለአምስት ፍሪኳንሲ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ማሰራጫዎች፣ ዩቱዩብ፣ እንዲሁም ኦንላይን ሚዲያ በአንድ ላይ ይተደደሩበታል፡፡
ቡድኑ ሌላው የተመለከተው በመገናኛ ብዙሃን ቅስቀሳ ሳቢያ የሚሊዮኖችን ህይወት ያሳጣውንና ለመታሰቢያ የተገነባውን የኪጋሊ መታሰቢያ ሙዚየም ነው፡፡በ1994 ዓ.ም የተካሄደውን የዘር ጭፍጨፋ ለመዘከር የተቋቋመውን ሙዚያም የህጻናትን ጭፍጨፋና በዓለም ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱትን የዘር ጭፍጨፋዎች ከሚዘክሩት ክፍሎች ውጪ አራት ክፍሎችን ይዟል፡፡ እነዚህም ክፍሎች፣ የርእዮተ አለም ግንባታ፣ የተካሄደውን ጭፍጨፋ የሚያሳይ፣ ለተካሄደው ጭፍጨፋ የተሰጠውን ምላሽ እና ድህረ ጭፍጨፋ የሚሉ ክፍሎች አሉት፡፡በስተቀር፣ በሙዚየሙ ውስጥ ምንም አይነት ፎቶግራፍ ማንሳት አይፈቀደም፡፡ እያንዳንዱ ሁነት በፎቶግራፍና በጽሁፍ ታጅቦ ተቀምጧል፡፡ ፎቶግራፉና ጽሁፎች ብቻ ሳይሆኑ አጫጭር ቪዲዮዎችም አብረው ተሰልፈዋል፡፡ ቦታ ሳይመርጡ የተከናወኑ ጭፍጨፋዎች አንድም ሳይቀር ተሰንደዋል፡፡ እያንዳንዱ መሪና አስተባባሪ የተናገራት ሁሉ፡፡ የመጀመሪያውን የጭፍጨፋ ግፉበት መልእክት ያስተላለፈው ሩዋንዳ የግል ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት ያስተላልፋቸው የነበሩ መልእክቶች፣ የሬዲዮ ጣቢያውን በባለቤትነት ለመቆጣጠር በአክስዮን የተደራጁ የአገር ውስጥና የአገር ውጪ ባለሃብቶች ካዋጡት የገንዘብ መጠን ጭምር ተሰንዷል፡፡ ለታሪክ እማኝነት፡፡ሙዚዩሙ የተገነባው ከ258.000 በላይ ሰዎች በተጨፈጨፉበት ስፍራ ነው፡፡
ሌላው በቡድኑ የተጎበኘው የሩዋንዳ ዩቲሊቲ ሬጉላቶሪ ኦቶሪቲ (Rwanda Utility Regulatory Authority) ነው፡፡ ተቋሙ ከራዲዮና ቴሌኮም ጋር የተያያዙ ተቋማትን የሚቆጣጠር ፖሊሲን መተግበር፤ፍቃድ መስጠት፤ፍትሃዊ የመገናኛ ብዙሃን ውድድር እንዲኖር ማበረታታትና ጥራት ያለው የስርጭት አቅም እንዲኖር ማገዝ ዋነኛ ተልዕኮዎቹ ናቸው፡፡
የልዑካን ቡድኑ በሩዋንዳ ቆይታው በሩዋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ዳባ ደበሌ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ ያቀረቡበት ዕለት ስለነበር ወደ አዲስ አበባ ከመመለሱ በፊት ዋዜማ በኪጋሊ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የራት ግብዣ ላይ ተገኝቷል፤
በዚሁ አጋጣሚም የልምድ ልውውጡን በተሳካ ሁኔታ ላካሄዱት የሩዋዳ ሚዲያ ኮሚሽን አመራር የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች የሚያሳይ በእጅ የተሰራ ስጦታ በአምባሳደሩ አማካይነት እንዲበረከትላቸው ተደርጓል፤
በማግስቱም የሩዋንዳ ሚዲያ ኮሚሽን አመራሮች ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ተጓዥ የሩዋንዳን ባህላዊ ስጦታ አበርክተው የልምድ ልውውጡ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል፡፡