ነሐሴ 15፣2013 ዓ.ም. (አዲስ አበባ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሚዲያዎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚመሩበት የእንባ ጠባቂና የግልግል ዳኝነት አካል የሚመራበትን የአሰራር ማንዋል አዘጋጀ፡፡
ነሐሴ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በግሮቭ ጋርደን በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አማረ አረጋዊ እንደገለፁት በምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 30 መሠረት ደንቡ የሚዘጋጀው በእንባ ጠባቂና በግልግል ዳኝነት አካል እንደሆነ ጠቅሰው ደንቡ በጽ/ቤቱ ድጋፍ ጨረታ በማውጣት በባለሙያዎች እንዲሰራ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የግልግል ዳንነት አካሉ ስራውን ሲጀምር የሚመራበት መመሪያ እንደሆነ የገለፁት አቶ አማረ በዕለቱ በሚደረገው ውይይት መጨመር ያለበት ወይም መቀነስ ያለበትን ጉዳይ ማንዋሉን ካዘጋጁት ባለሙያዎች ጋር እንድትወያዩ መድረኩ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
በደንቡ በአጠቃላይ ለግልግል ዳኝነት አካል አቤቱታ የሚቀርብበት፣ ክርክር የሚካሄድበት፣ ውሳኔ የሚሰጥበትና ይግባኝ የሚመራበት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የግልግል ዳኝነት አካሉ የስነምግባር መርሆዎች፣ የእንባ ጠባቂው ስልጣን እና ተግባር፣ የይግባኝ ሰሚ የዳኝነት አካሉ ስልጣን እና ተግባር፣ ከቅሬታው ጋር ተያይዘው መቅረብ ያለባቸው ማስረጃዎች፣ ቅሬታን ስለመመርመር እና ውሳኔ ስለመስጠት፣ በይግባኝ ሰሚ የዳኝነት አካሉ በቀጥታ ስለሚታዩ ጉዳዮችና ቅሬታ የመመልከት ሂደቱ የሚቋረጥበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የእንባ ጠባቂና የግልግል ዳኝነት አባላት በቀረቡት የሕግ ማብራሪያዎችና አስተያየቶች ላይ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን የግልግል ዳኝነቱ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ የሕግ ባላሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ፊሊጶስ አይናለም በሰጡት አስተያየት የማንዋሉ ርዕስ አጭርና ግልፅ ሆኖ ቢቀመጥ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡
የግልግል ዳኝነቱ እንባ ጠባቂ ዶ/ር ንጉሴ ተፈራ በበኩላቸው የደንቡ መዘጋጀት የግልግል ዳኝነት አካሉ ወደ ስራ ለመግባት እንደሚያስችለው ጠቅሰው በደንቡ ዙሪያ የምክር ቤቱ አባላት ተመሳሳይ ግንዛቤ የሚይዙበት መድረክ ሊዘጋጅ ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህርትና የግልግል ዳንነት አካሉ አባ የሆኑት ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ በበኩላቸው ግልፅነት ሊፈጠርባቸው ይገባል የሚሉ አንቀፆችንና በኤዲቲንግ መስተካከል ያሉባቸውን ጉዳዮች በማንሳት እንዲስተካከሉ ለባለሙያዎቹ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ ውይይት ላይ ከግልግል ዳኝነት አካል አባላት ለቀረቡ አስተያየትና ጥያቄዎች በባለሙያዎቹ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በመጨረሻም በሰነዱ እንዲካተቱና ተስተካክለው ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡