ወቅታዊ መግለጫ  የአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ ‹ መንግስታት ለሰብአዊ መብት እና ለፕሬስ...

  የአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ ‹ መንግስታት ለሰብአዊ መብት እና ለፕሬስ ነፃነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ሊያረጋግጡ ይገባል ›

ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/

(ሚያዝያ 252015 ፤አዲስ አበባ )  የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፤

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ አማካይነት በየዓመቱ ሚያዝያ 25 ወይም ሜይ 3 የሚከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን  በተለያዩ የዓለም ሀገራት በጦርነትና የህዝቦች መፈናቀል ሳቢያ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ስጋት በተከሰተበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃንና የፕሬስ ነፃነት አቀንቃኞች ዕለቱን በተለየ መልክ ይመለከቱታል፡፡

የአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን የዛሬ 30 ዓመት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ አማካኝነት በናሚቢያ ዋና ከተማ ዊንሆክ  በተካሄደው ኮንፍረንስ በየዓመቱ በመላው ዓለም በዚህ ቀን እንዲከበር ሲወሰን  መንግስታት በገቧቸው አለም አቀፍ ግዴታዎች መሰረት የፕሬስ ነፃነት እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ እንዲሁም ጋዜጠኞችና  ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  ለሙያው ስነ ምግባር እንዲተጉ ለማሳሰብ ነው፡፡

እለቱ መንግስታት ለሰብአዊ መብት እና ለፕሬስ ነፃነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ የሚያስታው ሲሆን  የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስለ ፕሬስ ነፃነት እና ሌሎች መብቶች ጉዳዮች መከበር  ቃላቸውን የሚያድሱበት ቀን ነው ።

የዘንድሮው የአለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን የሚከበረው ‹የወደፊቱን መብት መቅረፅ፤ የንግግር ነፃነት ለሁሉም የሰብዓዊ መብቶች መከበር አንቀሳቃሽ ነው › ወይም   “Shaping a Future of Rights: Freedom of expression as a driver for all other human rights.” በሚል መሪ ቃል ሲሆን ዜጎች  ሃሳባቸውን በነፃነት መግለፃቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ህጋዊ እውቅና ላገኙ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ መከበር ያለውን ጠቀሜታ  በማጉላት ላይ ያተኮረ   ነው፡፡

ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱት ጉልህ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች፣ በፀጥታ ሃይሎች  የተፈፀመውን ያለፍርድ እስር ጨምሮ፣ ህገወጥ ወይም የዘፈቀደ አፈናን የሚያሳዩ እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አይነት ተቋማት  ያወጧቸው ሪፖርቶችን መነሻ በማድረግ ለመነጋጋር ቀኑ ዕድል ይሰጣል።

መንግስት ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዙ የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ተግባራቱ ሁሉ ግን ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን  በማያጠብና የዜጎችን የዲሞክራሲያው ስርዓት ተሳትፎ በማይጎዳ መልኩ ሊሆን ይገባል፤ ማናቸውም ሕግን የማስከበር ተግባራትም በሕግ አግባብ ብቻ መመራት ስላለበት  ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መሠረት እንዲኖረው መንግስት  ሕገ መንግስታዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ፡፡

ሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳዮች የሚጠበቁት እና አጀንዳ የሚሆኑት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ባለው ጠንካራ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። ሆኖም መገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን ሲያስተላለፉ ከሀሰተኛ ዜና፤ከጥላቻ ንግግር፤ከብሔርና ከሐይማኖት ወገንተኝነት ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚስፈልግ በመሆኑ ጋዜጠኞች ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል፤ሕግን የሚተላለፉና የሌሎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚጥሱ የሀገርን አንድነትና ሰላም የሚያናጉ መገናኛ ብዙሃንንም የማጋለጥ ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል እንላለን፡፡

በመጨረሻም ጋዜጠኝነት ይበልጥ ሙያውን ያከበረ  ስነ ምግባሩን የጠበቀ፤ ጋዜጠኞች ከስጋትና ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች  ነፃ ሆነው የሚሰሩበት እንዲሁም ዜጎች ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙበት እሳቤ የሚያጎላበት  ቀን ሆኖ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ  ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ሚያዝያ 25 ቀን 2015 አዲስ አበባ፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe