ዜና”የተጻፈ ህግ ባይኖረንም፣ ምን ማድረግ እንደሌለብን እናውቃለን” ጃክሊን ሙማባሲ የሩዋንዳ ሮያል ኤፍ...

”የተጻፈ ህግ ባይኖረንም፣ ምን ማድረግ እንደሌለብን እናውቃለን” ጃክሊን ሙማባሲ የሩዋንዳ ሮያል ኤፍ ኤም 94.3 ባልደረባ

”የተጻፈ ህግ ባይኖረንም፣ ምን ማድረግ እንደሌለብን እናውቃለን” ጃክሊን ሙማባሲ የሩዋንዳ ሮያል ኤፍ ኤም 94.3 ባልደረባ

በአጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር)

ከሩዋንዳ እንዴት ይቀራል?!

Travel story for Rwanda
Travel story for Rwanda

ባለፈው መጋቢት ወር የጉዞ ሰነዶቼን በማዘጋጀት ሂደት ከጎበኘኋቸው ቢሮዎች መካከል በአንዱ ውስጥ ያስተናገደኝ ኃላፊ፣ “ኪጋሊ በጣም ንጹህ፣ በውሃ መውረጃ ቱቦዎች መካከል እንኳን ተቀምጠሽ ምግብ ብትበይ ምንም የማይመስልሽ ከተማ ናት” ሲለኝ፣ ሄደህ ነበር? ብዬ ጠየቅሁት። “አይ በሚዲያ ነው ያየሁት፣ ቢቢሲ ላይ” ነበር ያለኝ። የዚህ ሰው አባባል ሁለት ቁምነገሮችን አስታወሰኝ። አንዱ ሚዲያ ለጥሩ ገጽታ ግንባታ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳለው ማመላከቱ ነው።

ዓለማችንንና ሁለንተናዋን የምንረዳው ከመገናኛ ብዙሃን በምናገኘው መረጃ ነው። ዓለምን ልናደንቃትም ልንታዘባትም የምንችለው በምናገኘው መረጃ ነው። ልክ በአሁኑ ሰዓት የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነትን የሚመለከቱ መረጃዎችን በገባን ልክ እየቆረጥንና እየቀጠልን ለመረዳት እንደምንሞክረው ሁሉ። ሁለተኛው ያስታወሰኝ ቁምነገር ደግሞ ለተማሪዎቻችን የምንጠቅሰውን “two step flow” የሚለውን የመገናኛ ብዙሃንን አሰራር መተንተኛ ንድፈ ሀሳብን ነው። ይህ ንድፈ ሀሳብ መሰረት ያደረገው፣ ሰዎች ሚዲያው የሚናገረውን በቀጥታ መውሰድ ሳይሆን፣ አዋቂ ናቸው ብለው የሚያምኑባቸው ምሁራን የሚናገሩትን፣ የሚተረጉሙትን ወይም የሚያብራሩትን የበለጠ እንደሚያምኑ ነው። የአስተናጋጇ አባባል በአዎንታዊ መልኩ ተጽእኖ አሳደረብኝ።

ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ የደረስኩት፣ በተገቢው የመግቢያ ፍተሻ ሰዓት ነበር። ስደርስ ግን፣ “አውሮፕላኑ ስለተቀየረ የተመዘገቡትን ሰዎች ሁሉ መጫን አልተቻለም፣ የሚችሉ ከሆነ ወደነገ ይዛወርልዎት” ተባልኩ። እንዴት ተደርጎ! ከስንት ሳምንት በፊት የተያዘ ፕሮግራም፣ ስንት ዝግጅት የተደረገበት እቅድ፣ እንዴት በቀላሉ ይሰረዛል?! “አልችልም፣ የላከኝም ሆነ የሚቀበለኝ ተቋማት ስራቸው ይስተጓጎላል” ስል ሙግት ጀመርኩ። ሩዋንዳ የምንጓዘው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከሩዋንዳ ሚዲያ ኮሚሽን ጋር ተቀናጅተው ባዘጋጁት የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብር ለመሳተፍ ነበር። የሰራሁት ስህተት በበይነመረብ ገጻቸው ላይ አለመመዝገቤና ጉዞዬን አለማረጋገጤ ይመስለኛል። ይህን ያረጋገጥኩት ትንሽ ቆይተው ከተቀላቀሉኝ የጉዞ ቡድን አባላት ነው።

ወደሩዋንዳ የሚጓዝ ሰው ቪዛ የሚመታለት መዳረሻይቱ ሩዋንዳ ምድር ከገባ በኋላ ነው። ስለሆነም ተጓዦች ቢያንስ ከአንድ ሰዓት ቀድመው መመዝገብና መረጃቸው በበይነመረብ ግንኙነት ኪጋሊ አውሮፕላን ጣቢያ መድረስ አለበት። ደግነቱ በጊዜ ቦሌ በመድረሴ ሰራተኞቹ ተሯሩጠው ጊዜው ከማለፉ በፊት ተጓዥ መሆኔን አረጋገጡልኝ። ሩዋንዳን ለማየት በጣም ጓጉቻለሁ። በዚያ ላይ ወቅቱ አገሪቱ የ1994ን የዘር ጭፍጨፋ 28ኛ አመት የምታስብበት ነው። ከዚህች ከዓለም በስፋቷ 149ኛ ደረጃ ላይ ከምትገኝ፣ ስሟ በዓለም ላይ እጅግ መግነን ከጀመረ ሶስት አስርት አመታት ሊሞላት ጥቂት ከቀራት አገር መቅረት አልፈለግሁም። አጋጣሚው ተገኝቶ ከኪጋሊ እንዴት ይቀራል?! ማስተካከያ ተደርጎ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር 810 ገባሁ። ከላይ እንደገለጽሁት ጉዞዬን ባለማረጋገጤ የወንበር ቁጥሬ ተሰርዞ ስለነበር፣ ሌላ ቦታ ተፈልጎልኝ ተቀመጥሁ።

የገበታ ወግ፣ የጦርነት ወሬ

አሁን ተረጋግቼ መካከለኛው ወንበር ላይ ተቀምጫለሁ። ከቀኜ የተቀመጡት መንገደኛ ፊታቸውን ወደመስኮቱ መለስ አድርገው ብዙ ዶላሮች ይቆጥራሉ። እኔ ለሆቴል የምከፍላቸውን ጥቂት ዶላሮች ለማግኘት ስንት ቦታ እንደረገጥኩ ሳስበው እኚህ ሰው ከግራና ቀኝ ኪሶቻቸው እያወጡ የሚቆጥሯቸውን ዶላሮች ሳይ ልዩነታችን ሰፋብኝ። እኔ ለጉዞ የተሰጠችኝን ብር ወደ ዶላር ለመቀየር የስንት ሰው ፊት አይቻለሁ። ደግነቱ ያለንበት የአገራችን ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዳላማርር አድርጎኛል። ከግራዬ የተቀመጡት ደግሞ ዶላር ቆጣሪውን ሰውዬ አሻግረው በትኩረት ይመለከታሉ። እርሳቸውም እንደእኔ የተገረሙ መሰለኝ። እኚህ ተሳፋሪ ከግዙፍነታቸው የተነሳ የወንበሩ ቀበቶ ስላልበቃቸው ማራዘሚያ ተሰጥቷቸው ነው የወንበር ቀበቷቸውን ያሰሩት። የመጀመሪያ መዳረሻችን ወደሆነችው ወደ ቡሩንዲ ለመድረስ ለሁለት ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች ያህል በሰማይ ላይ መንሳፈፍ ጀመርን።

ጣፋጭና ትኩስ ምግብ ቀረበልን። “ዶሮ ወይስ የበሬ ስጋ?” እያለች ትጠይቃለች፣ አስተናጋጇ። አንዱ ተሳፋሪ፣ “አሳ እፈልጋለሁ እባክሽ” አሉ። “ይቅርታ ለዛሬ አሳ የለም። ከፈለጉ አትክልት አለ” ስትል መለሰች። አሰብ አደረጉና ዶሮ ተቀበሏት። የጉዞ ትኬታቸውን ሲገዙ የምግብ ምርጫቸውን አላስመዘገቡም ማለት ነው አልኩ፣ ለራሴ። ከቀረቡት የምግብ አይነቶች መካከል አንዱን አነሱና፣ “ይህ ምንድነው?” አሏት አስተናጋጇን። “ትንሽ ሩዝ አለው፣ ኩስኩስ ይባላል” አለቻቸው። ከሄደች በኋላ “ስኳር ላለበት ሰው ይሆናል?” ሲሉ ጠየቁኝ። እርግጠኛ ባልሆንኩበት ጉዳይ መናገር አልሻምና፣ “እርግጠኛ አይደለሁም፣ ይቅርታ” አልኳቸው። ከቀኜ ያሉት ሰው ጣልቃ ገቡና፣ “ስንዴ አለው፣ ግን ሽርክት ስለሆነ ለስኳር ህመምተኛ መጥፎ አይደለም። ኩስኩስ ይባላል። ልክ እንደፓስታ ነው” ሲሉ መለሱ። ቀጠሉና ስለቀረበልን ስለእያንዳንዱ ምግብ አስረዱን። የገበታ ወግ ተጀመረ። ከምግብ በኋላ ስጠይቃቸው ከ100 በላይ የሆኑ የምግብና አስተናጋጅነት ማሰልጠኛዎች ከሚገኙባት ደቡብ አፍሪካ የአንዱ ኮሌጅ መምህር መሆናቸውን ነግረውኛል። ንግግራቸው ብዙ የቱሪስት መዳረሻዎችና የበርካታ ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነችው አገራችን በየእለቱ የሚበስሉትን የባህል ምግቦች በማዘመን ረገድ ዘመናዊ የሆቴል ትምህርት ቤቶች መስፋፋት እንደሚገባቸው አሳሰበኝ።

እኚህ ደቡብ አፍሪካዊ መንገደኛ ከቶጎ መልስ ወደሩዋንዳ እያቀኑ ነው። ሌላኛው ደግሞ፣ ሜሪላንድ የሚኖረውን ልጃቸውን ጎብኝተው ወደቀያቸው ወደብሩንዲ እየተመለሱ ነው። የለበስኩትን የአገር ልብስ እየተመለከቱ፣ “ከየት ነሽ?” ሲሉ ጠየቁኝ ቡሩንዲያዊው:: “ከኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ” አልኩ። ትንሽ ቆዩና፣ “ጦርነቱ አለቀ እንዴ?” ሲሉ ያልጠበቅሁትን፣ መልሱንም የማላውቀውን ጥያቄ ሰነዘሩ። በእነዚያ ሽርፍራፊ ሰኮንዶች ውስጥ አእምሮዬ ስንት ቦታ እንደረገጠ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው። ንግግራችን መቀጠል ስላለበት፣ “አልቋልም፣ አላለቀምም” አልኳቸው።

የተለያየ መልስ ሊሰጠው የሚችል ጥያቄ ነው። ፖለቲከኛው አንድ ነገር ሊል ይችላል። የማህበራዊ ሳይንቲስቱ ሌላ። የሰላምና የፍትህ ባለሙያ ደግሞ ሌላ ሊል ይችላል። በበኩሌ የገባኝ ለእኚህ ሰው በጥንቃቄ የምመልሰው ጥያቄ መሆኑን ነው። ከጦርነት ውጭ አለመሆናችንም የታወቀ ነው። እዚያም እዚህም ግጭቶች አሉ። ሰዎች ይሞታሉ፣ ሰዎች ይፈናቀላሉ። ድርቅ ዙሪያ ዙሪያችንን ያናጥርብናል። ስራ አጥነትና ድህነትም ራሱን የቻለ ጦርነት ነው።

ዘንድሮ የእርሻ ስራቸው የተስተጓጎለባቸው በርካታ ገበሬዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፣ አውቃለሁ። የኑሮ ውድነት፣ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች እንደገና እንዲፈተኑ የተወሰነበት፣ ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት ያልቻሉ ተማሪዎች ጉዳያቸው እንደገና ተጢኖ እንዲገቡ የተወሰነበት። ይህ ሁሉ ጦርነት አይደል እንዴ? እንቅልፍ የሚያጣ ብዙ ነው።

በኪጋሊ ቆይታችን ይህ መልእክት በየስፍራው ተሰቅሎና ተለጥፎ ተመልክተናል። የዛሬ 28 ዓመት የተፈጠረውን ታሪካቸውን ላለመርሳት ጊዜው ሲደርስ እንዲህ ያስቡታል። ለማንኛውም ጠያቂዬ ቡሩንዲያዊ እዝን ብለው ከንፈራቸውን መጠጡ። አልቋልም፣ አላለቀምም ስትይ ምን ማለትሽ ነው? ብለው ማብራሪያ አልጠየቁኝም። ምንስ ቢሆን አፍሪካውያን አይደለን? ቀላልና ከባድ የኅብረተሰብ ጥያቄ ለይተን እናውቃለን።

ትንሽ ቆዩና ወዴት እንደምሄድ ጠየቁኝ። ኪጋሊ አልኩ። “ኪጋሊ በጣም ቆንጆ ከተማ ናት” ሲሉ አከሉ። ኪጋሊ በጣም ንጹህና ከአውሮፓ ከተሞች የምትነጻጸር እንደሆነች ገና ከአዲስ አበባ ሳልነሳ እንደሰማሁ ቀደም ሲል ጠቅሻለሁ። ኪጋሊ በብዙዎች አእምሮ እንድትሳል ያደረጋት ሌላም የክፍለ ዘመኑ ሁነት አለ።

EMC delegation
EMC delegation

አንድ ጎረቤቴ ወደ ኪጋሊ እንደምሄድ ስነግረው፣ “ከሩዋንዳ ብዙ ትምህርት ይዘሽ እንደምትመጪ እርግጠኛ ነኝ፣ በጋዜጣም ትጽፊልናለሽ” ያለኝ ማሳሰቢያ ትዝ አለኝ። አክሎም የአይማኩሌ ኢባጊዛን Left to tell አንብቤ እንደሆነ ጠይቆኝ ነበር። እርሱ የሚለውን መጽሐፍ ሙሉውን ባላነበውም፣ ከባለታሪኳ ጋር የተደረገውን ቃለመጠይቅ ከየመገናኛ ብዙሃኑ ተከታትያለሁ። ቃለመጠይቋን ብቻ ሳይሆን ባለመስቀል ጥልፍ የአገራችንን አጓጉል ስፌት የአበሻ ቀሚስ ለብሳ ስለአገሯ ፍጅት ትውስታዋን በየመድረኩ ስትናገርም በቪዲዮ ተመልክቻለሁ። ለማንኛውም ግን የ1994ቱን (እ.አ.አ) የሩዋንዳውያንን እልቂት ታሪክ ያልሰማ አይኖርም። ስለመገናኛ ብዙሃን የአፍራሽነት ሚና ሲነሳ፣ ስለጥላቻ ንግግርና መዘዙ ሲወሳ ከጀርመኑ የሂትለር ዘመን ቀጥሎ ሩዋንዳ ትነሳለች። የሩዋንዳ ማንነት ላይ የተመረኮዘ ጭፍጨፋን አስመልክቶ የተሰሩ የጥናት ወረቀቶች ብዙ ናቸው።

አረንጓዴይቱ ኪጋሊ

ተበታትነን ተቀምጠን የነበርነው የልዑክ ቡድን አባላት ከአውሮፕላን ስንወርድ ተገናኘን። ከዋልታው ሥራ አስኪያጅና ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ጋር ተልእኮዋችንን ጀመርን። ኪጋሊ ስንደርስ ሃይለኛ ዝናብ እየጣለ ነበር። ወደበጋ እየተጠጉ መሆናቸውን የምናርፍበት ሆቴል ተቀባይ አስረዳችን። ዝናቡ ሞቅ ያለ ቢሆንም፣ ቅዝቃዜ ግን አልነበረም። ከአዲስ አበባ ከመነሳቴ በፊት ዝናብ እንዳለ ስላነበብኩ፣ ዣንጥላ ይዣለሁ። ነገር ግን የጉዞ ሻንጣዬ ውስጥ ተቆልፎበታል። ተቀባያችን ትልቅ ዣንጥላ ይዛ ስለነበር፣ ለሶስት እንግዶች ስለማይበቃ ለእኔ ቅድሚያ ተሰጠኝና አስጠለለችኝ። በአገራችን ታላቅን ማክበር ደምብ አይደል!

በቆየንባቸው አራት ቀናት ላገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ የሆንን ሳይመስለን ኪጋሊን ከላይ እስከታች አየናት። እድሜ ለሩዋንዳ ሚዲያ ኮሚሽን፣ ኢሜልዳን መድቦልን ከእርሷ ጋር ሽር ስንል ሰነበትን። እውነትም ውብ ከተማ። በአራቱም ማዕዘናት አረንጓዴ። ጎዳናዎቹ በእቅድ የተሰመሩ። እንዲሁም ንጹህ። ነዋሪዎቹ ሁሉ በስራ ከላይ ወደታች የሚወጡ የሚወርዱ። ጀንበር ጠልቃ እንኳን የገበያ ስፍራዎቹ በንግድ የደመቁ።

መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ በኮረብታዎች የተሞላች ናት አገሪቱ። የ1000 ኮረብቶች ምድር ነው የምትባለው (Land of thousand hills)። በከተማይቱ ረባዳ ስፍራች ላይ ውሃ ገብ የመሬት ቁርስራሽ አንዳንድ ስፍራዎች ተንጣለዋል። ሰዎች ወደነዚያ አካባቢዎች ሄደው እንዳይሰፍሩ ይከለከላሉ፣ ምክንያቱም አካባቢው ረግረጋማና አስጣሚ ስፍራ ስለሆነ ለሰዎች ደህንነት አስጊ በመሆኑ እንደሆነ ኢሜልዳ ነግራናለች። በኪጋሊ የሚገኙ ሀበሻና ላሊበላ የተባሉ ሁለት የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶችን ሳይቀር ጋብዛ አሳይታናለች።

መገናኛ ብዙሃንና ሩዋንዳ

ከላይ በርእሴ የጠቀስኩትን አባባል የተናገረችው፣ ከጎበኘናቸው የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መካከል የሮያል ኤፍ ኤም 94.3 ባልደረባ ጃክሊን ሙምባሲ ናት። ሮያልኤፍ ኤም በማውንት ኬንያ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኝ እጅግ ተደማጭ ሬዲዮ ጣቢያ ነው። ሩዋንዳ ውስጥ ወደ 36 የሚጠጉ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ይገኛሉ። ሁሉም ሬዲዮ ጣቢያዎች የየራሳቸው የይዘትና የትኩረት አቅጣጫዎችን እየተከተሉ የሚሰሩ ናቸው። ጃክሊንን “የ1994 ዓ.ም የሩዋንዳን ታሪክ እናስታውሳን። እና ሬዲዮ ጣቢያችሁ ወደዚያ አይነት ሁኔታ እንዳይመለስ ወይም ታሪክ እንዳይደግም የምትተዳደሩበት ህግ አለወይ” ብዬ ጠየቅኋት።

የዩኒቨርሲቲውም ተማሪዎች ሆኑ የሬዲዮ ጣቢያው ተቀጣሪ ጋዜጠኞች፣ የጥላቻ ንግግርን ላለመድገም የሚመሩበት ደምብ ይኖራቸዋል ብዬ ገምቼ ነበር። ምላሽዋ የዘገየ፣ ነገር ግን ደግሞ አጭር ነበር። “የተጻፈ መመሪያ የለንም። ነገር ግን ማድረግ የሌለብንን ነገር ጠንቅቀን እናውቃለን። ሁልጊዜ በስራችን ሂደት ያ ጊዜ እንዳይደገም ጥንቃቄ እናደርጋለን” ነበር ያለችው። ቀጠለች፣ “ሰዎችን የሚያስቀይም፣ አንዱን ከሌላቸው የሚያበላልጥ መልእክት ማንም በፍጹም ይዞ አይመጣም” አለችን። ጋዜጠኞች በህገ ልቡና የሚመሩባት አገር ሆናለች ሩዋንዳ። ከዚያ በኋላ በሄድኩበት ሁሉ “እንዴት ነበር?” የሚል ጥያቄ አላነሳም። ወደ ሩዋንዳ ጄኖሳይድ ሙዚየም (Kigali Genocide Memorial) በሄድን ጊዜ የጥያቄውን መልስ አግኝቼዋለሁ።

ዛሬ ላይ የሩዋንዳ ጋዜጠኞች የሚጨነቁት፣ ስለሙያዊ ስነምግባር አተገባበር፣ ተቋሞቻቸውን ስለማዘመን፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መንገዶች መካከል የሚገጥማቸውን ፉክክር አሸንፎ ስለመውጣት ነው። የሬዲዮና የቴሌቪዥን መገናኛ ብዙሃን ሙያተኞችና ባለቤቶች የሚያሳስባቸው ከዲጂታል ሚዲያና ከማህበራዊ ሚዲያ በኩል ስላለውና ተደራሲዎቻቸውን ስለሚሻማቸው ጉዳይ ነው። በእነዚህ የዲጂታል ሚዲያዎች የሚመጣው ሌላም ነገር ያስሰባቸዋል። ሀሰተኛ መረጃ መሰራጨቱ፣ የወጣቱ ትውልድ ከማንበብ መራቁ፣ በእድሜ የገፋው ትውልድ አባላትን የሚያረካ መገናኛ ብዙሃን አለመኖሩ ነው።

ወደጀመርኩት ልመለስ። ወደመታሰቢያ ሙዚየሙ ያቀናነው፣ በከተማዋ መካከል በሚገኘው ካሜሊያ በተሰኘ ካፍቴሪያ ምሳችንን ከተመገብን በኋላ ነው። ተመግበን ስንወጣ ከመካከላችን አንዱ ለአንዲት እመጫት የኔ ብጤ አንድ ሺህ የሩዋንዳ ፍራንክ መጸወታት። አንድ የአሜሪካ ዶላር ወደ አንድ መቶ አስር ሺህ የሩዋንዳ ፍራንክ ይመነዘራል። ኢሜልዳ ተቆጣች። መንግስት ችግረኞች ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ካነሰም የእለት ጉርሳቸውን እንደያሟሉ ጥረት እንደሚያደርግ፣ የልመና ሳይሆን ሰርቶ የማደር ባህልን እንደሚያበረታታ አስረዳችን። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ብዙ የኔብጤዎችን በየመንገዳችን ያላየነው።

ወደ ሙዚየሙ እንደገባን አጭር ቪዲዮ ተመለከትን። ይህ የዘጠኝ ደቂቃ ቪዲዮ በ1994 (እ.ኤ.አ) ከሚያዚያ እስከ ሰኔ አጋማሽ የተፈጠረውን ጭፍጨፋ፣ ጥሎት ያለፈውን ጠባሳ የሚያሳይ መንደርደሪያ ነው። ይህ ቪዲዮ በእንግሊዝኛና በኢንኬንያሩዋንዳ ቋንቋ የተጻፉ የግርጌ ማስታወሻዎች ወይም ጽሁፋዊ ትረካዎች አሉት። የድምጽ ትረካ ለሚፈልጉ ጎብኚዎች የማዳመጫ መሳሪያ ይሰጣቸውና ትረካውን ማዳመጥ ይችላሉ። ለዚህ 15 የአሜሪካን ዶላር ይከፍላሉ። ክፍያው ሙዚየሙን ለመደጎም ይውላል። ጽሁፎቹን እያነበቡ መረዳት የሚፈልጉት ጎብኚዎች ግን ይህን ተጨማሪ ክፍያ አይጠየቁም።

ከውጭ ካልሆነ በስተቀር፣ በሙዚየሙ ውስጥ ፎቶግራፍ ማንሳት አይፈቀደም። ቢፈቀድ ኖሮ፣ ከነነፍሳቸው ወደወንዝ ተጥለው የሞቱ ሰዎችን አስከሬን አወጣጥ ሂደት፣ በገጀራ የተሰነጠቁ ጭንቅላቶችን ፎቶ፣ በየጥሻው የወደቁ የሰው ልጆችን አስከሬኖች እቀርጽ ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለወላጆቻቸው የነገ ተስፋ የነበሩና የተቀጩ ህጻናትን ሁኔታ በምስል አጋራ ነበር። በእናቶቻቸው እቅፍ ውስጥ እንዳሉ ከእናቶቻቸው ጋር በጥይት የሞቱ፣ ባዩትና በተመለከቱት ሰቆቃ ብዛት ተሰቃይተው የሞቱ ህጻናት ብዙ ናቸው።

እያንዳንዱ ፎቶግራፍ በጽሁፍ ታጅቦ ተቀምጧል። ፎቶግራፉና ጽሁፎች ብቻ ሳይሆኑ አጫጭር ቪዲዮዎችም አብረው በግድግዳዎች ላይ ተሰቅለው አጫጭር ትእይንቶችን ያሳያሉ። ከ28 አመት በፊት ከሚያዚያ እስከ ሰኔ የተከናወኑ የሰቆቃ ውርጅብኞች አንድም ሳይቀር ተሰንደዋል። መሪዎችና ልሂቃንን ጨምሮ፣ የመጀመሪያውን የጭፍጨፋ ግፉበት መልእክት ያስተላለፈውን ከዚያ ጊዜ አንድ አመት ቀደም ብሎ የተመሰረተው ሩዋንዳ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በባለቤትነት ለመቆጣጠር በአክስዮን የተደራጁ የአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ባለሃብቶች ካዋጡት የገንዘብ መጠን ጭምር ተሰንዷል።

በባለሃብቶች የተመሰረተውና ለሁለት አመታት ወጣቶችን በስነልቦና ሲያዘጋጅ፣ እንዲሁም ጭፍጨፋው እንደተጀመረ ነዳጅ እየጨመረ ህዝብ ሲያፋጅ የነበረው ሚዲያ ታሪክ ከሙዚየሙ ይዘቶች አንዱ ነው። ዋነኛ ደጋፊና ከ500 ሺህ በላይ ገጀራ ወደአገሪቱ እንዲገባ ያደረጉት የአገሪቱ ጎምቱ ባለሀብት በየአገሩ ተደብቀው ሲኖሩ ቆይተው ከ26 አመት በኋላ ፈረንሳይ አግኝታ ለጦር ፍርደኝነት እንዳስረከበቻቸው ሰነዶች ያስረዳሉ።

ግጭትና ጥላቻ የአንድ ጀምበር ክስተት አይደለም

ሙዚየሙ ውስጥ ያሉትን የታሪክ ማስታወሻዎች ሁሉ ተመለከትኳቸው። ኢሜልዳ ትከተለኛለች። ጓደኞቼ ተመስጠው በየጥጉ እየሄዱ ሕይወት አልባ ኗሪ የታሪክ ምስክሮችን ይመለከታሉ። ኢሜልዳ ከቆምኩበት ቦታ ዘወር ብዬ ወደሌላው ክፍል እንድሄድ ትመራኛለች። ሰቅጣጭ ድርጊቶችን በጥሞና ቆሜ ስመለከት የስሜቴ መጎዳት ይታያታል መሰለኝ፣ ከዚያ ስፍራ እንድነቃነቅ ታደርገኛለች።

ሙዚያሙ የተለያዩ ክፍሎች አሉት። የህጻናትን ጭፍጨፋና በዓለም ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱትን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎች ከሚዘክሩት ክፍሎች ውጭ በእኔ አረዳድ አራት ክፍሎችን ተመልክተናል። የመጀመሪያው ርእዮተ አለም ግንባታን የሚያሳይ ክፍል ነው።

ይህ ክፍል የግጭት ጥንስስ የተፈጠረበትን ሂደት ነው የሚተርከው። በጀርመንና በቤልጂየም ቅኝ ገዢዎች ከፋፍለህ ግዛ መርህ የተፈጠረ እንደሆነ ህያዋን እማኞችም ሆኑ ሰነዶች ይመሰክራሉ። ተመሳሳይ ቋንቋና ተመሳሳይ ባህል ያላቸውን የሩዋንዳ ዜጎች ቅኝ አገዛዝ እንዴት ለሁለት ቡድን እንዲከፈሉ እንዳደረጋቸው ይተርካል። እሳቤው ወይም ርዕዮተ ዓለሙ ለመግዛት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ቢሆንም፣ አተገባበሩ ግን ሁለት መንገዶችን የተከተለ ነው። የመጀመሪያው ምጣኔ ሀብታዊ ገጽታ እንዲኖረው በማድረግ ነው። ለምሳሌ እንደገባን የሚጀምረው ሰነድ የሚነግረን፣ ከ10 በላይ ላሞች ያላቸውን በአንድ ጎራ፣ ከ10 በታች ላሞች ያላቸውን ደግሞ በሁለተኛው ጎራ በመክፈል ልዩነት እንዲያቆጠቁጥ መደረጉን ይተርካል። ሁለተኛው መንገድ ደግሞ አካላዊ ገጽታን መሰረት ያደረገ ክፍፍል ነው የሚሉ አሉ። አይማኩሌ ኢባንጊዛ አንዷ ናት። ይህች ከሞት ያመለጠች ሩዋንዳዊ በሃይማኖታዊ መነጽር ሁሉም ሩዋንዳውያን ልዩነት የሌላቸው የአምላክ ፍጡራን ቢሆንም፣ ሰዎች ግን አካላዊ ልዩነትን መሰረት በማድረግ ለሁለት እንደከፈሏቸውና አንዱን ሰይጣን አንዱን መልኣክ እንዳደረጓቸው ታስተምራለች።

ይህኛው አቀራረብ ሩዋንዳውያንን በፊት ቅርጽና በቁመታቸው ተመርኩዘው ሁለት የተለያዩ ፍጡራን “መሆናቸውን” እንዲቀበሉና “እኛ እና እነርሱ” በሚል በጎራ እንዲለያዩ እንዳደረጋቸው የሚያመለክት ነው። ይህ የኢኮኖሚ ገጽታንና አካላዊ ልዩነትን መሰረት ያደረገው ከፋፍለህ ግዛ ርእዮተ አለም፣ በሩዋንዳውያን መካከል የእርስ በርስ ጥላቻና ንቀት እንዲያቆጠቁጥ ስለማድረጉ ይነገራል። በቁጥር አነስ ያሉትና ከ10 ላሞች በላይ ማካበት የቻሉት ያለውን የሃብትና የስልጣን እርከን እንዲቆጣጠሩ ያደረጉት ቅኝ ገዢዎች ናቸው የሚለው ታሪካዊ ማስረጃ ብዙ ነው።

ቀስ በቀስ ሁኔታዎች ወደከፋ ገጽታ እየተቀየሩ መጡ። ክፍፍሉ እዚህም እዚያም ግጭቶችና ትንንሽ ትንኮሳዎች እንዲከሰቱ አደረገ። አዝማሚያው ያላማራቸው ሩዋንዳውያን ወደ ጎረቤት አገር ብሩንዲ መሸሽ የጀመሩት እ.ኤ.አ ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ ነው። የኢኮኖሚ ልዩነቱና የኑሮ ውድነቱ ስር እየሰደደና እየጎላ ሲመጣ መኖር ያቃታቸውና በርካታ ቁጥር ያላቸው ሩዋንዳውያን ኢኮኖሚውን የተቆጣጠሩትንና በቁጥር የሚያንሱትን ለማጥፋት መከጀል፣ መነሳሳት፣ ከዚያም አልፎ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ። በ1973 ሁለተኛው ምዕራፍ የዘር ጭፍጨፋ እንደተካሄደ ተዘግቧል። የ1994ቱ ከፍተኛው ነው።

ሁለተኛው የሙዚየም ክፍል የሚያተኩረው እዚህኛው የታሪክ ምእራፍ ላይ ነው። የኢንተርሃሞይ ስልጠናዎች፣ ጥላቻን የሚያባብሱ የመገናኛ ብዙሃን ስብከቶች እየተጧጧፉ ሄዱ። የርእዮተ አለም ግንባታው ጎልብቶ አንዱን የበላይ፣ ሌላውን የበታች አድርጎ የማስቀመጥና የአንድ አገር ዜጎች እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩና እንዲጠላሉ ማድረግ የተቻለበት የዘመቻ ምእራፍ ነው። በጊዜው የነበሩት የአገሪቱ መሪ በስደት ላይ ከሚገኙት የመንግስት ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር (በአሁኑ ፖል ካጋሚ ከሚመራው) ስምምነት አድርገው ሲመለሱ፣ የተሳፈሩበት አውሮፕላን እንዲጋይ ተደረገ።

ወዲያውም ቀደም ሲል ወጣቶችን በሙዚቃ አለማምዶ፣ ሁቱዎቹ ቱትሲዎቹን እንዲጨርሷቸው መልእክቱን ማሰራጨት ጀመረ። ሙዚዩሙ የታነጸበት ይህ ስፍራ በዚያ ስፍራ ብቻ የተጨፈጨፉትን ከ250000 በላይ ሰዎች ለመዘከር ነው። በ”ሆቴል ሩዋንዳ” ፊልም እንዳየነው የጭፍጨፋው ትእዛዝ መጀመሪያ የተሰጠበት ሆቴል በዚያው አቅራቢያ ይገኛል።

ሌላው ጅምላ ጭፍጨፋ የተካሄደበት በከተማዋ የሚገኘው ስታዲየሙ ነው። አብያተ ክርስቲያናትም የዚህ አይነቱ ተግባር መከወኛ ከመሆን አልተረፉም። ሸሽተው በዚያ የተጠለሉ ህጻናትና አረጋውያን የተጨፈጨፉበት ቤተክርስቲያን ለመታሰቢያ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አጠገቡ ሌላ ለአምልኮ የሚጠቀሙበት አዲስ ቤተክርስቲያን ተገንብቷል። በመቶ ቀናት ውስጥ ከ80 ሺህ በላይ ቱትሲዎችና ቱትሲዎችን የሚደግፉ ለዘብተኛ ሁቱዎች አልቀዋል። ሌላው ቀርቶ የሁቱ አባል የሆኑት የወቅቱ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትርም በለዘብተኛነታቸው ተገድለዋል። ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሩዋንዳውያን ወደጎረቤት አገሮች ተሰደዋል። ከመቶ ቀናት በኋላ ጦርነቱ የቆመው ዛሬ ሩዋንዳን እየመሯት በሚገኙት የቀድሞው የሩዋንዳ መንግስት ተቃዋሚ ቡድን መሪ በፖል ካጋሜ አማካኝነት፣ እንዲሁም በፈረንሳይ አጋዥነት ነው።

ሶስተኛው የሙዚየም ክፍል የሚያሳየው፣ ለተካሄደው የዘር ጭፍጨፋ ከዓለም ኅብረተሰብና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከታላላቅና ከሃይማኖት አባቶች የተሰጠውን ምላሽ ነው። ክስተቱ የእርስ በርስ ጦርነት ነው የሚለውን የቅኝ ገዢዎች አገላለጽ ያጋጠሙኝ ሩዋንዳውያን አይቀበሉትም። ሁቱ አጥቂ፣ ቱትሲ ተጠቂ ሆነው ቢከፈሉም በድርጊቱ ውስጥ ግን ግፍ የደረሰባቸው ሰብዓዊነት ያላቸው ሁቱዎችና ለጥቃት ተነጥለው የተሳሉት ቱትሲዎች መሆናቸው ይነገራል። አይማኩሌ እንደጻፈችው፣ ሁቱነት፣ በቁመት አጠርና በቆዳ ቀለም ደመቅ ያለ ጥቁረት መያዝ፣ አፍንጫ ማጠር ማለት ነው። ቱትሲነት ደግሞ በቁመት ዘለግ ማለት፣ አፍንጫ ሰልከክ ማለት ነው ትላለች። ቁመቷ እንዳይረዝምባት ባለተረከዝ ጫማ ማድረግን ሁሉ ትፈራ እንደነበር በሕይወት ታሪኳ ጠቅሳለች።

ያለቁት ሁሉም ሩዋንዳውያን ናቸው። በጉብኝታችን ወቅት አብሮ ሲያንሸራሽረን የነበረው በወጣትነትና በጎልማሳነት እድሜ መካከል የሚገኘው አሽከርካሪ፣ በወቅቱ የሰባት አመት ልጅ እንደነበረና፣ እናቱ ወደ ጎረቤት አገር አምልጣ እንደተረፈች፣ የአባቱ ወገኖች ግን በጭፍጨፋው እንዳለቁ ነግሮኛል። ጣቱን የሚቀስረው በወገኖቹ ላይ ሳይሆን፣ ለዚህ ምክንያት በሆኑት የውጭ ቅኝ ገዢዎች ላይ ነው። ከተባበሩት መንግስታት ጀምሮ የተለያዩ የዓለም ተቋማት፣ የሃይማኖት አባቶች የተናገሩትና የከወኑት ለፍጅቱ አቀጣጣይ እንደነበሩ ተዘግቧል።

አራተኛው የሙዚያሙ ክፍል የሚያሳየው ደግሞ ድህረ ጭፍጨፋ የነበረውን ክንውን ነው። አይማኩሌ እንደጻፈቸው ማን ማንን እንደገደለ፣ በምን አይነት መሳሪያና በምን አይነት አኳኋን እንደገደለ፣ ሁሉም የዚያን ወቅት ሩዋንዳውያን ያስታውሳሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ድህረ ፍጅት ያለውን ሁኔታ ማስተካከል እጅግ ከባድ ነበር። ግን ያንን ክብደት ሩዋንዳውያን ራሳቸው ተወጥተውታል። የሚጠየቀው እንዲጠየቅ ሆኗል። አብሮ ለመኖር የልብ ስብራትና ቂምን ለመፋቅ የተጠቀሙት የራሳቸውን ባህል፣ እንዲሁም የመጨረሻውን ንጹህ የሰውን ህሊናና ይቅርባይነትን ነው። ወጣቱ ትውልድ ደግሞ የልዩነትን ግድግዳ እየገነደሱ ጋብቻ በመፈጸም፣ አብረው በመሆን ሩዋንዳ ከገባችበት አዘቅት ቶሎ ወጥታለች። ከዚያ በኋላ አገር ግንባታ ነው የተካሄደው። እርቅና ሰላም ግንባታ ነው የተካሄደው። ዛሬ ማንም ሩዋንዳዊ፣ “እኔ የዚህ ወገን ነኝ” አይልም፣ ልጆች ሁሉ “እኔ ሩዋንዳዊ ነኝ” ነው የሚሉት።

ከጉብኝቱ ስንወጣ “ሌፍት ቱ ቴል”ን እዚያው አገኘሁት። ከዚያ ስሜት ሳልወጣ በሁለት ሌሊቶች አንብቤ የጨረስኩት። በዚያ እውነተኛ ግልሰባዊ ታሪክ ውስጥ ያነበብኩት ሰብዓዊነት በእጅጉ የተሞገተበት፣ ቂምና ጥላቻን ከውስጥ አውጥቶ ለመጣል የተፈተኑበትን ትርክት ነው። ቀደም ሲል የጠቀስኩት ጎረቤቴ፣ “እኛ አገር እንደዚያ አይነት እንዳይመጣ ነው ስጋቴ” ያለኝ በጆሮዬ አቃጨለ። በአፍህ ማር ይግባበት ማለት ይኖርብኛል።

ሰዎችን ለዚያ አይነት የሚያጋልጡ ጉዳዮችን መገናኛ ብዙሃን ከመነካካት ተጠንቅቀው መስራት ይኖርባቸዋል። ሰውን ማዕከል ያደረጉ ትርክቶች ሁሉ የሰውን ልጅ ታላቅነት የሚሰብኩ መሆን ይኖርባቸዋል። የመልካም አስተዳደርና ኢፍትሃዊነትን መዋጋት ማለት ሰዎችን በውስጣቸው ጥላቻና መጠራጠር እንዲፈጠር ማድረግ አይደለም። ይልቁንም በአብሮ መኖር ሂደት ውስጥ ሰውን ከክብሩ የሚያሳናሱትን፣ ህሊናውን የሚጎዱትን፣ በራስ መተማመኑን የሚያኮስሱትን ድርጊቶች መዋጋት ተገቢ ነው።

ከሩዋንዳ የመገናኛ ብዙሃን ኮሚሽን ሰዎች የሰማሁትን እዚህ ላይ መጥቀስ ይኖርብኛል። ኮሚሽኑ ከሚመራባቸው መርሆች መካከል “ይበልጥ ግልጽነት በተንሰራፋ መጠን ተጠያቂነት ይጎለብታል። ጋዜጠኞች ፖለቲከኞች እንዲሆኑ አትፍቀዱላቸው፣ ሚናን ማደበላለቅ ስህተት ነው። ማንኛውንም ታሪክ ስትዘግቡ በተጠያቂነትና በኃላፊነት ስሜት መሆን አለበት። እርግጥ ነው፣ መገናኛ ብዙሃን ለገቢ የሚሰሩ ናቸው። በውስጣቸው የሚያቅፏቸው ሰዎች ግን ሙያተኛ ጋዜጠኞች መሆን አለባቸው።”

ሩዋንዳውያን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚቆጣጠሩበት፣ ጥፋትን ከመስራት የሚጠባበቁበት ስርአት አላቸው። እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ወደሙያው ከመግባቱ በፊት በሁለት መንገዶች ሙያውን መተዋወቅ አለበት፣ ወይ ከዩኒቨርሲቲ በሙያው መመረቅ፣ ወይም ደግሞ ስልጠና ማግኘት። የተሰባሰቡት በዚህ መንገድ ነው። አንድ ጋዜጠኛ ከፍተኛ ጥፋት ቢያጠፋ በመተዳደሪያ ደምባቸው መሰረት የሙያ ፈቃዱን የሚነጠቀው በሩዋንዳ ሚዲያ ኮሚሽን በኩል ነው። ደግነቱ እስከዛሬ ለዚህ የተዳረገ ሙያተኛ የለም። ሁሉም ራሳቸውን ተቆጣጥረው ይሰራሉ።

ከጉዞ መልስ

ለጦርነት ወሬ ብዙም የራቅን አይደለም። ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድን አንብቤያለሁ። ታላላቆቻችን የሚዘከሩበትን ማማ በሰማይን አንብቤያለሁ። የአምስት አመቱን የኢትዮ-ኢጣልያ የጦርነት ዘመን ታሪክን የሚዘክሩ ጥቂት መጻህፍትን አንብቤያለሁ። የመገናኛ ብዙሃን እንዴት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ እንደሚሆኑ የሚያሳየውን የፕሮፓጋንዳ ሞዴል ንድፈ ሀሳብን ከተማሪዎቼ ጋር አጥንቻለሁ። አሁን ደግሞ በምክንያት የአይማኩሌ ኢሊባጊዛን ለወሬ ነጋሪን ወይም Left to Telln አነበብኩ፣ ከታተመ ከ6 አመት በኋላ። ባለታሪኳ ከቱትሲ ወገን ሆና በመቆጠሯ ልትገደል ስትታደን፣ የሁቱ ወገን የሆኑት ካህን በቤታቸው ከልጆቻቸውም እንኳን ደብቀዋት ለሶስት ወር እንዴት እንዳተረፏት ትተርክልናለች። አባቷ ከመገደላቸው በፊት ነፍሷን እንድታተርፉ የላኳት በ”ሮሳ”ም ሆነ በሃይማኖት አንድ ወዳልሆኑት ካህን ዘንድ ነበር። “ምንም እንኳን ልዩነት ቢኖረንም እርሱ እንደማይገድልሽ አውቃለሁ” ብለው ነበር። እውነታቸውን ነበር። በየምዕራፉ ከሞት ጋር ሲፋጠጡ የምትነግረን ልብ ቀጥ ያደርግ ይመስላል።

አይማኩሌን በአካል ባገኛት፣ “መኖርሽ፣ ከሞት መትረፍሽ ለምክንያት ነበር። ዛሬ ብዙዎች ካንቺ ታሪክ ሰምተው እንዲማሩ በቀጥታ መንገር ነበረብሽ፣ እንኳንም እግዚአብሔር በአውሎም በወጀቡም አሳልፎ አዳነሽ። እንደገና መኖር እንደሚቻል አሳየሽ” እላት ነበር። በታሪኳ ውስጥ የጠቀሰቻቸው የ91 አመቷ አዛውንት ያሏትን እንደጻፈችው “ይቅር የማይባለውን ይቅር ማለትን አስተማርሽን”።

ለይቅርታ ጊዜና ወቅት የለውም። ምን ጊዜም ምእራፉ ክፍት ነው። ለዚህ ደግሞ ሚዲያዎች አምዶቻቸውን፣ የአየር ሰዓቶቻቸውን ማዋል ይጠበቅባቸዋል። በውዥንብር ውስጥ ያለውን አዲስ ትውልድ አእምሮ የሚያረጋጋ፣ የወደፊት እጣ ፈንታን ብሩህነት የሚፈነጥቅ ስራ መስራት ያስፈልጋል። ክፉውንና ደጉን በመለየት፣ አገርና ዜጎችን የሚታደግ ስራ መስራት ያስፈልጋል። ይልቁንም ማህበረሰባዊ ኃላፊነትን ለመወጣትና ንቅዘትን፣ ኋላቀርነትን፣ ሙስናን፣ የመልካም አስተዳደር እጦትን፣ ራስ ወዳድነት፣ ስንፍናን የሚያጣጥሉና፣ በራስ መተማመንን፣ የስራ ክቡርነትን ሂሳዊ በሆነ አቀራረብ ማስተማርን ወቅቱ ይጠይቃል።

አጋረደች ጀማነህ

አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2014

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe