ዜናየሶማሌ ክልል የጋዜጠኞች ማኅበር 80ሺህ ብር ተበድሮ የታሰሩ አራት አባላቱን በዋስ አስፈታ

የሶማሌ ክልል የጋዜጠኞች ማኅበር 80ሺህ ብር ተበድሮ የታሰሩ አራት አባላቱን በዋስ አስፈታ

የሶማሌ ክልል የጋዜጠኞች ማኅበር በአስር ላይ የነበሩ አራት የነበድ ቴሌቪዥን ባልደረባ የሆኑ አባላቱን የ80 ሺህ ብር ዋስትና አቅርቦ ከእርስ እንዲወጡ ማድረጉን ገለጸ።

ከጂግጂጋ ከተማ በሶማሊኛ ቋንቋ ለተመልካቾቹ የሚደርሰው የነበድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሠራተኛ የነበሩት አራት ጋዜጠኞችን ታስረው የነበሩት ከሳምንታት በፊት ነበር።

ማኅበሩ አባላቱን ከእስር ለማስፈታት ለዋስትና የሚያስፈልጋቸውን 80 ሺህ ብር ከከተማው ባለሃብት ተበድሮ በመክፈል አርብ ዕለት እንዲለቀቁ ማድረጉን ለቢቢሲ ገልጿል።

ኅዳር 01/2014 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ ነበረ ኢብራሂም ሁሴን፣ ሰልማን ሙክታር፣ ሙሐመድ ቃሲም እና ሂርሲ ሞሐመድ የተሰኙት ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ይህንንም ተከትሎ ኅዳር 03/2014 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ጋዜጠኞቹ ፖሊስ በጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለተጨማሪ 10 ቀናት በእስር እንዲቆዩ ጉዳያቸውን የተመለከተው ችሎት ፈቅዶ ነበር።

ከአስር ቀን በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቀሩት ጋዜጠኞቹ ከአራት ቀን በኋላ ማለትም ሕዳር 17 ፖሊስ ይዟቸው ችሎት ቢቀርብም ፋይላቸው ባለመቅረቡ ጉዳያቸው ሳይታይ መቅረቱ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የቆየው የማኅበሩ አባል አብድራዛቅ ሼክ ሐሰን ይናገራል።

በመቀጠልም ካለፈው ሳምንት ሰኞ ኅዳር 27 እስከ ረቡዕ ድረስ በተከታታይ ችሎት ቀርበው ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ ክሱን ማሰማቱን አብድራዛቅ ይናገራል።

በማስከተልም ረቡዕ ዕለት ጋዜጠኞቹ የዋስትና ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ከእስር ቢፈቱ ተቃውሞ እንደሌለው በመግለጹ ችሎቱ ጋዜጠኞቹ በዋስ እንዲፈቱ ወስኗል።

ለጋዜጠኞቹ ጠበቃ ማቆምን ጨምሮ ጉዳያቸውን በቅርበት ሲከታተል የቆየው የክልሉ የጋዜጠኞች ማኅበርም ለእያንዳንዳቸው የተጠየቀውን 20ሺህ ብር ከግለሰብ ተበድሮ መክፈሉን ታግሯል። ይህንን ተከትሎም ጋዜጠኞቹ አርብ መፈታታቸውን የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አያን ሽኩሪ ኦስማን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

አያን የጋዜጠኞቹ አሰሪ ጋዜጠኞቹ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ የቀረበባቸውን ክስ አስመልከቶ ያሉ ወጪዎችን ሊሸፍን ሲገባው እናንተ እንዴት የጠበቃ እና የዋስታ ወጪዎችን ለብቻችሁ ልታወጡ ቻላችሁ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

“እኛ እንደ ሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማኅበር ማንኛውም ጋዜጠኛ ግዴታውን እንደሚወጣው ሁሉ መብታቸውን የማስከበር ግዴታ አለብን። ስለዚህ መርጠን ያደረግነው ሳይሆን ግዴታችንን ነው የተወጣነው” ሲሉ አያን ተናግረዋል።

“ምንም እንኳን አቅም ባይኖረንም ሕጋዊ እና ጠንካራ ማኅበር እንደመሆናችን ለዋስትና ያስፈለገንን ገንዘብ በብድር አግኝተን ጋዜጠኞቹን ለማስለቀቅ ችለናል። በቅርቡም የአባላት መዋጮ በማድረግ ገቢ እናሰባስባለን” ሲሉ አያን ተናግረዋል።

የነበድ ቴሌቪዢን ሥራ አስኪያጅ የሆኑት እና የቀድሞዋ የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ፊልሰን አብዱላሂ ወላጅ አባት አቶ አብዱላሂ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ለማግኘት አልቻልንም።

አቶ አብዱላሂ እና አራቱ ጋዜጠኞችን ለእስር የዳረገው በጣቢያው የተላለፈ ይዘት እንደነበር ይታወሳል። አቶ አብዱላሂ በፖሊስ በቁጥጥር ስር በዋሉ ማግስቱ መለቀቃቸውን ልጃቸው ፊልሰን በትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸውም አይዘነጋም።

በወቅቱ የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማኅበር የጋዜጠኞቹን መታሰር ተከትሎ “እርምጃው በክልሉ እየተሻሻለ የመጣውን የነጻ ሚዲያ መስፋፋት ያቀጭጫል። መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት እንዲያከብር፣ የታሰሩት ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንዲሁም ጣቢያው ወደ ሥራው ይመለስ” ሲል ጠይቆ ነበር።

የማኅበሩ መሪ አያን በድጋሚ መንግሥት የጋዜጠኞችን መብት እንዲያከብር፣ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ የጋዜጠኞች ማኅበራት ደግሞ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ምንጭbbc amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe