የምክር ቤቱ የግልግል ዳኝነት ቡድን በ18 አባላት ተደራጅቶ ወደ ሥራ ቢገባም መፍትሔ ፈልገው እየመጡለት ያሉት ጉዳዮች የሚዲያ ተቋማትንና ጋዜጠኞችን የሚመለከቱ አለመሆናቸውን፣ በምክር ቤቱ የግልግል ዳኝነት ሰብሳቢ አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም አስታውቀዋል፡፡
በአገራዊ የፀጥታ ሁኔታ አለመመቸትና በፋይናንስ እጥረት ሳቢያ ለሁለት ዓመታት ያህል ሳይካሄድ መቆየቱ የተነገረለት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ፣ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ፣ ‹‹የግልግል ዳኝነት የሚሰጡ አካላት በቢሮ ደረጃ የተደራጁ ቢሆንም፣ ክሶች ወደ ምክር ቤቱ እየመጡ አይደሉም፡፡ የጋዜጠኞች ጉዳይ ወደ ምክር ቤቱ ብቻ ሳይሆን፣ ክሶችም ወደ ፍርድ ቤት እየሄዱ አይደለም፡፡ አንዳንዴ ጋዜጠኞችን በተመለከተ ፍርድ ቤት ሄደን ስንጠይቅ አናውቅም ይላሉ፣ አዋሽ አርባ ነው ያለው ሲባል ይሰማል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ አማረ ወደ ምክር ቤቱ ለመፍትሔ የሚመጡት ጉዳዮችን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ‹‹አንዳንድ ጊዜ ከቤቴ አፈናቀሉኝ፣ የከፈልኩበት ኮንዶሚኒየም አልደረሰኝም የመሳሰሉ አቤቱታዎች ይመጣሉ፡፡ ምክር ቤቱን የማይመለከቱ በመሆናቸው በቀጣይ ማስታወቂያ መሥራትና ማስተማር ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹የአገሪቱ ሕግ ማንኛውም ሰው ሲከሰስ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ አውቆት ነው ፍርድ ቤት የሚቀርበው ቢልም፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችን ለመጠየቅ ፖሊስ ዘንድ ስንሄድ አናውቅም ይባላል፡፡ ፍርድ ቤት ስንሄድም እኛ የት እንደታሰሩ አናውቅም ይላሉ፤›› ብለዋል፡፡
ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መደንገጉንና ጋዜጠኛ ሐሳቡን ሲገልጽ ጥቃት እንዳይደርስበት መንግሥት ከለላ ማድረግ እንዳለበት ቢቀመጥም፣ አሁን ግን ጥቃቱ መባባሱንና ከለላ አለመኖሩን አቶ አማረ አስረድተዋል፡፡
የግልግል ዳኝነት ሰብሳቢው አቶ ፊሊጶስ፣ ‹‹ምክር ቤቱ የሚመጡለትን አቤቱታዎች ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ፣ ባለጉዳዮችም ወደ ፍርድ ቤት ሳይሄዱ ችግራቸው እንዲፈታ ጉዳያቸውን ወደ ምክር ቤቱ ሊያቀርቡ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ጋር የተገናኘም ሆነ መሰል የጋዜጠኝነት ሥራ ጋር ጉዳይ ያላቸው ለምክር ቤቱ የግልግል ዳኝነት በማቅረብ አስገዳጅ የሆነ ውሳኔ አናገኝም የሚል እምነት ስለሚይዙ፣ ጉዳያቸውን ወደ መደበኛው የፍትሕ ተቋም እንጂ ወደ ምክር ቤቱ ይዘው እንደማይመጡ ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ኃይሉ በበኩላቸው፣ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች በግልግል ዳኝነት መታየት የነበረባቸውን ሁሉንም ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱ ተመልክተናል ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በጣም ልምድ ያላቸው የግልግል ዳኝነት ባለሙያዎች ያለ ሥራ መቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹በጣም ትልቅ ድግስ ተደግሶ፣ ምግቡና መጠጡ ተዘጋጅቶ ታዳሚ ግን የለም፣ ምን ይደረግ?›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ፍርድ ቤት ስንሄድ አሁንም የሚመላለሱ ጋዜጠኞች እንዳሉ እንሰማለን፡፡ የእርስ በእርስ ቁጥጥር መፍትሔ ስለሚያስገኝ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት ምክር ቤቱን ሊጠቀሙበት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የግልግል ዳኝነት ሰብሳቢው አቶ ፊሊጶስ ሲያብራሩ፣ አቤቱታ አቅራቢዎች በምክር ቤቱ የሚታይ ጉዳይ ላይ የሚወሰነው ቅጣት በመንግሥት ተቋማት ከሚሰጠው ውሳኔ ጋር ጠንካራ አይሆንም የሚል ሥጋት እንዳላቸው እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን የእርስ በእርስ ቁጥጥር የሚዲያ ተቋማት በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርተው የሚገዙበትን፣ የሙያ ሥነ ምግባርና የመልካም አሠራር ደንብ የሚያወጡበትን፣ የዘርፉን የሙያ ብቃት የሚያሳድጉበትና የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ቅሬታዎች የሚያስተናግዱበትን አሠራር በመዘርጋት ራሳቸውን ለሕዝቡ ተጠያቂ በማድረግ፣ እርስ በርስ የሚተራረሙበት ሒደት መሆኑ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ተደንግጓል፡፡
አቶ አማረ የምክር ቤቱን ሪፖርት ሲያቀርቡ የምክር ቤቱ አባላት ከሆኑ ሚዲያዎች መካካል ዓመታዊ መዋጮ በመክፈል ግዴታቸውን እየተወጡ ያሉ ጥቂቶች መሆናቸውን፣ ብዙዎች ከአቅም ማነስና አንዳንዶች ደግሞ ከተነሳሽነት ጉድለት ክፍያ እየፈጸሙ አይደለም ብለዋል፡፡ ይህም በአባላት ዘንድ የባለቤትነት መንፈስን የሚያቀዘቅዝ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመው፣ የመንግሥት ሚዲያዎችም በበጀት የሚተዳደሩ ሆኖ እያለ በጀት ይዘው እየፈጸሙ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ከጥቂት ዓመታት በፊት ወገግ ያለ ተስፋ የነበረው ቢሆንም፣ እንደገና እያሽቆለቆለ መምጣቱ በጣም ያሳስባል፤›› ያሉት አቶ አማረ፣ የነፃነት ምኅዳሩ እየጠበበ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ተግዳሮትና የጋዜጠኞች የሙያ ነፃነት ጉዳይ ሳይሆን አካላዊ ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ተስተውለዋል ብለዋል፡፡ አክለውም ከጋዜጠኞች እስርና ወከባ ባሻገር፣ በአንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ቢሮዎች ላይ የቁሳቁስና የመሣሪያ ዝርፊያ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ ወ/ሮ ትዕግሥት ይልማ ባለፉት ዓመታት የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ በመግባታቸውንና የኅትመት ዋጋና የሳተላይት ክፍያ በመጨመሩ ምክንያት፣ አብዛኞቹ የሚዲያ ተቋማት አደጋ ተጋርጦባቸው የተወሰኑት ለመዘጋት ደርሰዋል ብለዋል፡፡ ለዚህ አሳሳቢ ጉዳይ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡