ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/
ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
‹ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የኮቪድ 19 ወቅታዊ ስጋት በሚመጥን ደረጃ መረጃዎችን በተቀናጀ ስልት ግንዛቤ የመፍጠር ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል›
(መጋቢት 23፤2013 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍና በሀገራ አቀፍ ደረጃ የህዝብ ስጋት የሆነው የኮቪድ 19 ወይም የኮሮና ተህዋስ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ ለመመከት ህዝብና መንግስት እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የምክር ቤታችን አባል የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ምንም እንኳ የተመሰረቱበት አላማ እና የኤዲቶርያል ቁመና ልዩነት ሊኖረው ቢችልም አሁን ከፊታችን የተጋረጠውንና የሁላችንም ስጋት የሆነውን ተህዋሲ ለመከላከል ግን በተቀናጀ መልኩ በጋራ መቆም እንዳለባቸው ያምናል፡፡
እንደሚታወቀው ወቅቱ ከምንም ጊዜ በላይ ፈጣን እና ተዓማኒ መረጃ ማቅረብ የሚያስፈለግበት ወቅት ነው፡፡ በተለይም የተህዋሱን ስርጭት ከመግታት አንጻር ህብረተሰቡን ማንቃት እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ ማስጨበት ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ብዙ ይጠበቃል፡፡ የኮሮና ተህዋሲ ወረርሽኝ ዓለምን በሚያሰጋበት በዚህ ወቅት እኛ የኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋማት ችግሩን እንደ ህዝብ ጠላት ተመልክተን በጋራ ልንመክተው ይገባል፡፡
የኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰሞኑን ባወጡት የኮቪድ 19 ምርመራ ሪፖርት ቁጥሩ በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን ያሳያል፡፡ እንደ አብነትም ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የኮቪድ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጤና ተቋም ሄደው ህክምና ላይ የነበሩ ፣ በማህበረሰብ ቅኝት እና ዳሰሳ አማካኝነት ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው፣ የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በጤና ተቋማት ናሙና የሰጡ እና ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ የኮቪድ-19 ምርመራ የተደረገላቸው ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ከ 7,659 ግለሰቦች ውስጥ በ1,981 ሰዎች ላይ ወይም ከ100 ግለሰቦች 26 (26%) ያህሉ ኮቪድ-19 ቫይረስ እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህም በወቅቱ ምርመራ ካደረጉ ከአስር ሰዎች ሶስቱ ወይም ከሶስት ሰዎች አንዱ በቫይረሱ መያዛቸውን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ200 ሺ በላይ ተሸግሯል፡፡
ይህ ማለት የበሽታው አጠቃላይ ስርጭት ማህበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታየው ቸለተኝነትና መዘንጋት ችግሩን ወደ ከፋ ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል። ስለሆነም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስጋቱን በሚመጥን ደረጃ መረጃዎችን በየዕለቱ በተቀናጀ ስልት ግንዛቤ የመፍጠር ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
በመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የሚያወጧቸውን መረጃዎች ለህብረተሰቡ በፍጥነት በመግለጽ ግለሰቦች፣ ህብረተሰቡ፣ የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ማህበራት እና ድርጅቶች መረጃውን በመጠቀም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት መጨመሩን በመረዳት ተገቢውን የበሽታውን መከላከያ መንገድ እንዲተገብሩ ለማስቻል መገናኛ ብዙሃን ከዚህ በታች ያለውን ምክረ ሀሳብ ቢያንስ ለአንድ ሳምንት እንዲተገብሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
1ኛ/ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የኮቮድ 19 ስርጭት በህብረተሰቡ ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑ ትኩረት ሊያገኝ በሚችል መልኩ በዜና፤ በማስታወቂያና በፕሮግራሞች ላይ ቋሚ የሆነ ሎጎ በማድረግ ህብረተሰቡ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግ፤
2ኛ/ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የኮቪድ 19 ጤና ነክ መረጃዎችን ራሱን በቻለ መልኩ ተለይቶ ‹ዜና ኮቪድ› ተብሎ እንዲቀርብ ማድረግ፤
3ኛ/ በዜና መግቢያና መውጫ ላይ የኮቪድ 19 መልዕክቶች ተሰርተው በእንዲቀርቡ ማድረግ፤
4ኛ/ የጋዜጣና መፅሔት ህትመቶች እንዲሁም የድረ ገፅ ሚዲያዎች በፊት ለፊት ገጾች ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ሎጎዎችን ወይም መረጃዎችን በማተም ህይወት የማዳን የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ለጥሪ እናቀርባለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ተገቢውን መረጃ ለህዝብ ከማድረስ አንፃር መንግስት ተከታታይ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ በሚዲያዎች በኩል የማቅረብ ፍጥነቱን እንዲያሻሽል እያሳሰብን፤ ምናልባት ችግሩ እየተባባሰ የሚመጣ ከሆነና የሰዎች እንቅስቃሴ በሌሎች አገራት እንደታየዉ በከፍተኛ ደረጃ የሚገታ ከሆነ የሚዲያ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ተገቢ መረጃ ማቅረብ ላይ ችግር እንዳይገጥማቸው መንግስት ከወዲሁ እንዲያስብበት ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
አፍን አፍንጫችንን በጭምብል እንሸፍን ! እጃችንን እንታጠብ! ርቀታችንን እንጠብቅ! የጤና ምክሮችን እንተግብር!
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ