ወቅታዊ መግለጫ‹የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ያገለለ የምክክር ሂደት ውጤታማ የመሆን እድሉ አነስተኛ በመሆኑ ሂደቱ...

‹የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ያገለለ የምክክር ሂደት ውጤታማ የመሆን እድሉ አነስተኛ በመሆኑ ሂደቱ እንደገና ሊጤን ይገባል›

ጋዜጣዊ መግለጫ/ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን አስቸኳይ /

(ሰኔ 12015 ፤አዲስ አበባ )  የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፤

ምክር ቤታችን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክር ኮሚሽን በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በአንክሮ እየተከታተለ ሲሆን ኮሚሽኑ በሀገራችን ውስጥ ለዘመናት ከኖሩ ቅራኔዎችና ቁርሾዎች  ጀምሮ በየጊዜው ለዜጎች ሞት፤ መፈናቀልና ንብረት ውድመት ምክንያት ስለሆኑ ጉዳዮች ድረስ ነቅሶ በማውጣት  ህዝባዊ ውይይትና ምክክር በማድረግ መፍትሔ ያበጃል የሚል እምነት አለን፤  ኮሚሽኑ ላለፉት ሁለት ዓመታት ራሱን በማደራጀትና ለምክክሩ አስፈላጊ የሆኑ የቅድም ዝግጅት ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ ተሳታፊዎች ልየታ ሂደት  መግባቱን ተረድተናል፤

ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ምክክር ያደረገ ቢሆንም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን እንደ ተቋም ከመጋበዝ ይልቅ ሌሎች ሲወያዩ የዜና ሽፋን እንዲሰጡ ብቻ የሚጋበዙ መሆኑ  ትልቅ ጉድለት ነው ብለን እናምናለን፤

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተዓማኒነትና ውጤታማነት ከሚለኩበት መስፈርቶች መሀከል አንዱ የተሳታፊዎች ልየታ ሂደት እና አተገባበር ዋናውን ቦታ እንደሚይዝ ይታመናል፤  ዜጎች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በውክልናም ሆነ በቀጥታ እንዲሳተፉ ሲደረግ የምክክር ሂደቱን አሳታፊነትና እና አካታችነት ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡

ሆኖም  የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች ልየታን በሚያካሂድበት ወቅት የምክክር ሂደቱ ዋናኛ ባለድርሻ አካላት የሚባሉት የፖለቲካ ፖርቲዎች ምክር ቤትን፤ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤን እንዲሁም ሌሎች በርካታ የሲቪክ  ማህበራትን ከግምት አስገብቶ ተሳታፊ ሲያደርግ የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራትንም ሆነ  የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን የሚወክለውን ምክር ቤቱን መዘንጋቱ  የአካታችነትን  መሰረታዊ መርሆን ይቃረናል ብለን እናምናለን፤ በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ያገለለ የምክክር ሂደት ውጤታማ የመሆን እድሉ አነስተኛ በመሆኑ ሂደቱ እንደገና ሊጤን ይገባል እንላለን፡፡

ሀገራዊ ምክክር በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ  ሂደቱ በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት ለህዝብ ሲተላለፍ /የቀጥታ ስርጭቶችን ጨምሮ/ መከተል ስለሚገባው ሥነ ምግባር ምክር ቤታችን በጥናት የተደገፈ ደንብ እያዘጋጀ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እየገለፀ ሀገራዊ  ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከዘጋቢነት ሚናቸው ባለፈ በሙያ ማህበራቱና በምክር ቤቱ  የተወከሉ ሙያተኞች ሀሳብ በአግባቡ እንዲንፀባረቅ እንዲደረግ  ሂደቱም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙዎችን የሀሳብ መዋጮ ከግምት እንዲያስገባ እንጠይቃለን፤

በመጨረሻም በቅርቡ የተከበረው የዘንድሮው የአለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን  ‹የወደፊቱን መብት መቅረፅ፤ የንግግር ነፃነት ለሁሉም የሰብዓዊ መብቶች መከበር አንቀሳቃሽ ነው › ” በሚል መሪ ቃል ሲሆን ዜጎች  በእንዲህ ያለ ሀገራዊ የምክክር መድረኮች ላይ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ ማበረታታት  በዓለም አቀፍ ደረጃ ህጋዊ እውቅና ላገኙ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ መከበር ሚዲያው ያለውን የማይተካ ሚና  ለማጉላት እንደሆነ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ሰኔ 1 ቀን 2015 አዲስ አበባ፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe