የመንግሥት አካላት በአምስት ቀናት ለሚዲያዎች ምላሽ እንዲሰጡ የሚል ድንጋጌ ይዟል
የመንግሥት አካላትን የሐሳብ ልውውጥ ሊያሰናክል የሚችል መረጃ ክልከላ ይጣልበታል
የመረጃ ነፃነት ኮሚሽን እንደሚቋቋም ይገልጻል
የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሕግ ማሻሻያ ሪፎርሞች አካል የሆነው ረቂቅ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ለባለድርሻ አካላት ውይይት ቀረበ።
በዓቃቤ ሕግ ሥር የተቋቋመው የሕግ ማሻሻያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አማካይነት ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት፣ በምክር ቤቱ ሥር ተደራጅቶ አዋጁን ካረቀቀው የባለሙያዎች ቡድን ጋር ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት አድርገዋል።
ለውይይት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ስለመረጃ ነፃነት አስፈላጊነት የሚገልጹ ማብራሪያዎችን በመግቢያ ሀተታው ላይ ያስቀመጠ ሲሆን፣ የመረጃ ነፃነትን በማረጋገጥ ሰብዓዊ መብቶችን ማረጋገጥ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መልካም ግንኙነትን መገንባትና ሙስናን መዋጋት አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29(3)(ለ) መረጃ የማግኘት መብትን በግልጽ ያረጋገጠ በመሆኑና የኢትዮጵያ መንግሥት የአስተዳደር ባህል በአብዛኛው ሚስጥራዊ በመሆኑ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀምንና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማስከተሉን በመረዳት፣ እንዲሁም የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከቱ ጉዳዮች ግልጽ እንዲደረጉና ውይይት እንዲደረግባቸው ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ረቂቁ መሰናዳቱን የረቂቁ መግቢያ ይገልጻል።
የመንግሥትና የግል አካላት ለግለሰቦችና ለመገናኛ ብዙኃን መረጃን ተደራሽ እንዲያደርጉ የሕግ ግዴታ ለመጣል፣ የሕዝብ ተሳትፎንና የሥልጣን ባለቤትነትን የማረጋገጥ፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ውጤታማነት የሰፈነበት የመንግሥት አሠራርንና መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር በመወሰንና የመረጃ ነፃነትን ማረጋገጥ ያለውን ከፍተኛ ሚና በመገንዘብ ረቂቁ መሰናዳቱንም ያስረዳል።
በዚህም ምክንያት በሥራ ላይ ያለውን የመረጃ ነፃነት ሕግ በማሻሻል የሕዝቡን መረጃ የማግኘት ፍላጎት በሚያንፀባርቅና መብቱን ይበልጥ መጠበቅና ማራመድ በሚያስችል አዲስ ሕግ መተካቱ አስፈላጊ መሆኑ በረቂቁ መግቢያ ተመልክቷል።
በረቂቁ ከተካተቱ ድንጋጌዎች መካከል በመገናኛ ብዙኃን ለሚቀርብ መረጃ የማግኘት ጥያቄ የመንግሥት አካላት ግዴታና ኃላፊነቶችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ለመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡበትን የጊዜ ገደብ ይወስናል።
የመገናኛ ብዙኃን ወይም መረጃን ለሕዝብ ማሠራጨት ዋነኛ ተግባሩ የሆነ አመልካች፣ በመንግሥት አካል ተከናውኗል ወይም በቅርቡ ሊከናወን ነው የሚባልና ሕዝብ በአስቸኳይ ሊያውቀው የሚገባ መረጃ ስለመሆኑ ተጨባጭ ምክንያታዊ መነሻ ያለው ጥያቄ ካቀረበ፣ የመንግሥት አካሉ እጅግ ቢዘገይ ከአምስት የሥራ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እንዳለበት በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል።
ይሁን እንጂ ይህ የመረጃ ጥያቄ የቀረበለት የመንግሥት አካል የመረጃ ኃላፊ የቀረበው የመረጃ ጥያቄ አጣዳፊ አይደለም ብሎ ካመነ፣ አመልካቹ አስተዳደራዊ ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል ምላሽ በመስጠት የመረጃ ጥያቄውን በ20 የሥራ ቀናት እንዲያስተናግድ ይደነግጋል።
መረጃ ጠያቂው በውሳኔው ካልተስማማ ለተቋሙ የበላይ አመራር አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችል፣ በበላይ አመራሩ ውሳኔ ቅር ከተሰኘም ለመረጃ ነፃነት ኮሚሽኑ ቅሬታ ሰሚ አቤቱታውን ማቅረብ እንደሚችል፣ በዚህም መረጃ የማግኘት መብቱ እንደተነፈገ ካመነ ለፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል የሚገልጹ ድንጋጌዎችን ረቂቁ አካቷል።
አቤቱታ የቀረበለት የበላይ አመራር ለአስቸኳይ የመረጃ ጥያቄ በአምስት የሥራ ቀናት ውሳኔ መስጠት እንዳለበት፣ በተመሳሳይ ለኮሚሽኑ በቀረበ የአስቸኳይ መረጃ ጥያቄ አቤቱታ ላይ ኮሚሽኑ በአምስት የሥራ ቀናት ምላሽ መስጠት እንዳለበት፣ የተገለጹትን ሒደቶች አልፎ ለፍርድ ቤት በሚቀርብ ይግባኝ ላይ ደግሞ፣ ፍርድ ቤቱ በ30 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት እንደሚኖርበት ረቂቅ ድንጋጌዎቹ ያመለክታሉ።
የአዋጁን ዓላማዎች ለማስፈጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሚሆን የመረጃ ነፃነት ኮሚሽን እንደሚቋቋምም የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል።
የኮሚሽኑ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያቋቋመው ገለልተኛ ኮሚቴ አማካይነት በረቂቁ የተገለጹ መሥፈርቶች ተመዝነው ብቁ የሆኑት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚቀርቡ ተመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መሠረት ከሚቀርቡለት የኮሚሽኑ አባላት መካከል ዋናና ምክትል ኮሚሽነሮችን በመምረጥ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሾሙ የሚያቀርብ መሆኑን የረቂቁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።
ለመረጃ ጠያቂዎች የማይሰጡ ወይም ጥበቃ የሚደረግላቸው መረጃዎችና ሰነዶችንም ሪቂቅ አዋጁ ይዘረዝራል። ከእነዚህም መካከል ጥበቃ የሚደረግላቸው የመንግሥት የሥራ ሰነዶችና መረጃዎች ምንነትና ክልከላ የሚጣልበትን አመክንዮ የሚዘረዝሩ ይገኙበታል።
በዚህም መሠረት የመረጃው መገለጽ ግልጽ የሆነ የሐሳብ ልውውጥን፣ ምክክርን፣ ሪፖርትን፣ የውሳኔ ሐሳብን ወይም ውይይትን በመገደብ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውስጥ ወይም በተለያዩ የመንግሥት አካላት መካከል የሚደረገውን የውይይት፣ ወይም የምክክር ሒደት ሊያስተጓጉል እንደሚችል የመረጃ ኃላፊው ያመነበትን የመንግሥት ሰነድ መከልከል እንደሚችል ይደነግጋል።
መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስተዳደር ያለውን አቅም ሊያዳክሙ የሚችሉ፣ የመንግሥት ድርጅቶችን የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚመለከቱ መረጃዎች እንዳይገለጹም የመረጃ ኃላፊው ጥበቃ ማድረግ ይችላል።
በሥራ ላይ ያለው የብድር ወይም የወለድ ተመንን፣ የጉምሩክ ወይም የኤክሳይስ ቀረጥን፣ የግብር ወይም ማናቸውም ሌላ የመንግሥት የገቢ ምንጮችን፣ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥርን ወይም ክትትልን፣ የመንግሥት ብድርን፣ የሸቀጦች ወይም የአገልግሎቶች ዋጋን፣ የኪራዮችን፣ የደመወዝ ወይም የቀን ክፍያዎችን ወይም ሌሎች ገቢዎችን የሚመለከቱ ቁጥሮችን የመለወጥ ወይም እንዳለ የመቆየት ውሳኔ ውጥኖችን እንዳይገለጹ ጥበቃ ከሚደረግላቸው መረጃዎች መካከል ናቸው።
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ክልከላ የሚጣልባቸው ወይም ጥበቃ የሚደረግላቸው መረጃዎች በተመለከተ የተቀመጠው የረቂቁ ድንጋጌ ለትርጉም የተጋለጠ በመሆኑ፣ ተፈጻሚነቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
ለመረጃዎች ጥበቃ እንዲደረጉ ተብለው የተገለጹት ምክንያቶች፣ ‹‹ማስተጓጎል ወይም ማሰናከል›› የሚሉ መሆናቸው ለትርጉም ክፍት እንደሆነ ገልጸዋል።
ገለልተኛ የመረጃ ነፃነት ኮሚሽን እንዲቋቋም በረቂቁ መቀመጡ ከቀደመው አዋጅ ትልቅ መሻሻል የታየበት እንደሆነ የጠቀሱት ተወያዮች፣ ይህ ድንጋጌ የመፅደቅ ዕድሉ ላይ ግን ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢዘጋጅም የባለድርሻ አካላት በተለይም የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን፣ በሕግ ማሻሻል ብሔራዊ ምክር ቤቱ ሥር የተዋቀረው የሚዲያ ሕግ ሪፎርም ቡድን አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ጎሹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተሳታፊዎች የቀረቡት ጠቃሚ አስተያየቶች እንደሚካተቱና በረቂቅ አዋጁ ላይ ተጨማሪ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ወደፊት እንደሚካሄድ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።