ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር የተሰጠ መግለጫ
~ ለዜጎች መብት መከበር የሚሟገተው ጋዜጠኛ መብት ይከበር፣
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት መሻሻል እያሳየ እንደነበር ማህበራችን እና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ሲመሰክሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና ይህ መሻሻል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሸረሸረ መሄዱን በብዙ ማሳያዎችን መግለጽ ይቻላል፡፡
ለአብነትም የሚከተሉትን ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡
1. በአንድ ወቅት የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ባልደረባ የነበረው ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ስቲዲዮ በሥራ ላይ እያለ ትጥቅ ባነገቱ የጸጥታ አካላት ወደ ሰንዳፋ ተወስዶ ታስሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በየትኛውም አግባብ የታጠቁ ኃይሎች ወደ መገናኛ ብዙኃን ስቱዲዮዎች ፈጽሞ መግባት እንደሌለባቸው እሙን ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ይህ ተደርጎ አይተናል፡፡
2. የአሐዱ ኤፍ ኤም ሬድዮ ባልደረባ የነበረው ጌጥዬ ያለው የታሰረ ባልደረባውን ለመጠየቅ ሰንዳፋ ፖሊስ ጣቢያ ባመራበት ወቅት የክልሉ ጸጥታ አካላት “ጋዜጠኞች መታሰር አለባቸው” በሚል እንዳሰሩት ሙሉ መረጃ አለ፡፡
3. የፍትሕ መጽሔት ማኔጅንግ ኤዲተር ተመስገን ደሳለኝ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከቢሮው ተወስዶ እና በእስር ቆይቶ ከቀናት በኋላ መለቀቁ ይታወሳል፡፡
4. የባላገሩ ቴሌቪዥን ጣብያ ባልደረባ ጋዜጠኛ አስናቀ ማርሸትም በኦሮሚያ ክልል አሌልቱ ከተማ “አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማትን የያዘ ልብስ ለበሳችሁ” በሚል ታስሮ ፍርድ ቤትም ሳይቀርብ መለቀቁ ይታወሳል፡፡
5. የአሐዱ ኤፍ ኤም ሬድዮ ባልደረባ ክብሮም ወርቁ በመንግስት ኃይሎች ተወስዶ የት እንዳለ ሳይታወቅ ቆይቶ ከወራት በኋላ ተለቋል፡፡ ይህ ጋዜጠኛን ማፈን እና መሰወር ከመንግስት የማይጠበቅ ድርጊት ነው።
6. የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውም ታስሮ ለወራት ከቆየ በኋላ ቢለቀቅም ንብረቶቹ ሙሉ በሙሉ በጸጥታ ኃይሎች እጅ ስር ይገኛሉ፡፡
7. ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድም ታስራ ፍርድ ቤት ሳትቀርብ ከአንድ ወር በላይ ቆይታ ተለቃለች።
8. “የአሸባሪውን ሸኔ ቡድንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ ነበር” ያላቸውን ሶስት ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች ማለትም አሚር አማን – የአሶሺየትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ፣ ቶማስ እንግዳ – የካሜራ ባለሞያ እና አዲሱ ሙሉነህ የፋና ብሮድካስቲንግ ጋዜጠኛ በቁጥጥር ስር አውሏል። በቅርቡም ጋዜጠኛ አዲሱ ሙሉነህ ከአንድ ወር ተኩል እስር በኋላ ሲለቀቅ ሌሎቹ በእስር ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በተጠርጣሪነት የተያዙት ጋዜጠኞች ወንጀለኛነታቸው በፍርድ ቤት ባልተረጋገጠበት ሁኔታና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሚደነግገው ውጭ አስቀድሞ እንደወንጀለኛ እንዲቆጠሩ በማድረግ ምስላቸው በሚዲያ እንዲሰራጭ በማድረግ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ተፈጽሞባቸዋል።
9. ሌላው የተራራ ኔትወርክ ዩትዩብ አዘጋጅ የሆነው ታምራት ነገራም ባልታወቀ ምክንያት ታግቶ እስካሁን ድረስ በገላን ከተማ እንደሚገኝ ማህበራችን ከቤተሰቦቹ አረጋግጧል። ንብረቶቹም በሙሉ በመንግስት ተወስደዋል፡፡ ታምራት ነገራ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እስካሁን በእስር ላይ መቆየቱ እጅግ አሳዛኝ እና ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑን ማህበራችን ያምናል፡፡
በአጠቃላይ ጋዜጠኞችን ካለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ እንዲሁም ይህንን ያህል ጊዜ እስር ቤት ማቆየት ከሕግም ከሞራልም ያፈነገጠ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ይህ ጉዳይ የተለመደ ሆኗል፡፡
ጋዜጠኛ የህዝብ አንደበትና ጆሮ በመሆኑ የሚያራምዳቸው ሀሳቦችን ከተለያዩ ምንጮች ሊያገኝ ስለሚችል የግል አቋም ተደርጎ መወሰዱ ብቻውን አግባብ አይደለም። ማንኛውም ጋዜጠኛ ወይም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ የሚታሰረው ለሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክት ይዘት ከሆነ ያስተላለፈው ሀሳብ የእርሱ ወይም የሌላ ሰው ሊሆን ስለሚችል እርሱ ብቻ በሀሳቡ ብቻ ሊጠየቅ አይገባም። ያም ሆኖ በዘገባ ወቅት የተፈጠረ የመረጃ እና/ወይም የእውነታ ስህተት ቢኖር እንኳን ተመጣጣኝ ማስተካከያ በዚያው ሚዲያ ላይ ማድረግ የሚችልበት አሰራር እያለ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደእስር መውሰድ ተገቢ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ ማንኛውም ጋዜጠኛ የመረጃ ምንጩን ምስጢራዊነት የመጠበቅ ሙያዊ መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ መንግስት ማጤን ይኖርበታል።
ጋዜጠኞች በታፈኑ ቁጥር የሀሳብ የበላይነት እየከሰመ የሀገሪቱ የፕሬስ ዕድገትም እየቀጨጨ ይሄዳል።
ማህበራችን ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ታስረው ሲፈቱ ችግሮች በሂደት ይስተካከላሉ የሚል ተስፋ የነበረው ቢሆንም ችግሩ ግን እየተባባሰ መሄዱን አረጋግጧል፡፡ ባለፉት አሰርት ዓመታት ጋዜጠኞች ሲታሰሩ፣ ሲሰደዱና ሲገደሉ ሁላችንም አዝነን ለሀገራችን የምንችለውን አድርገን ለውጥ መምጣቱ ቢታወቅም ለውጡ ግን ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የተለየ ነገር ይዞ አልመጣም። በመሆኑም ጋዜጠኞች ሙያዊ ነጻነታቸውን ሳያጡ እንዲሰሩ ሊፈቅድላቸው ሲገባ በተደጋጋሚ ማሰርና ማንገላታቱ መቆም እንዳለበት እናሳስባለን፡፡
መንግስት ጋዜጠኞችን መጠየቅና ማብራሪያ መጠየቅ ሲፈልግ በሀገሪቱ ሕግ እንዲሁም ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም ዓቀፋዊ ስምምነቶች መሰረት የተፈራረመቻቸውን መብቶች ግምት ውስጥ አስገብቶ ሊሆን ይገባል፡፡ በመርህ ደረጃ አንድ ጋዜጠኛ፣ አንድ መሃንዲስ፣ አንድ ሚኒስትር እኩል መሆኑን ማመን ያስፈልገናል፡፡
ይህ ማለት ግን አጥፊ ግለሰቦችና ባለሙያዎች ሲኖሩ በሕግ አግባብ እንደማንኛውም ዜጋ ሊጠየቁ ይገባል። ይህ ሲሆን ግን ፈጸሙት በተባለው ድርጊት በሕግ አግባብ ብቻ የሚጠየቁበት አግባብ ተከብሮ፣ በትክክለኛው ጊዜ ክስ ተመስርቶባቸው፣ በሕግ ጥላ ስር ባረፉበት ቦታ በቤተሰቦቻቸው የመጠየቅ መብታቸው ተከብሮላቸው ሊሆን ይገባል።
ጋዜጠኞች አሁን ባለው ሁኔታ እየተሳደዱ የሚቀጥሉ ከሆነ አዲሱ ትውልድ የጋዜጠኝነትን ሙያ እንደወንጀል እየቆጠረ ከሙያው እንዲሸሽ የሚያደርግ፣ ባለሙያው በሚሰራው ስራ ነጻ ሆኖ ከመስራት ይልቅ እንዲሸማቀቅ የሚያደርግ፣ የምንናፍቀው የፕሬስ ነጻነትም ሆነ የሀገር ብልጽግና ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ስለሚያደርግ ለብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ድምጽ ለሚሆነው ባለሙያ ክብር ይሰጥ እንላለን፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
የካቲት 2014 ዓ.ም