ዜናከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ፤ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/

ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ፤ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያካሄዱ ያሉትን የተዛባ ዘገባ ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ በመሆኑ ሊታረም ይገባል፤

(ህዳር 252014 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤

የምክር ቤታችን አባል የሆኑ የሚዲያ ተቋማት   ምንም እንኳ የባለቤትነት ይዞታቸውና የተመሰረቱበት  አላማ ልዩነት ያለው ቢሆንም ሀገራችን አሁን የገጠማትን ፈተና ለመወጣት እውነተኛ፤ ትክክለኛና ወቅታዊ ዘገባዎችን ለህብረተሰቡ ከማቅረብ ጎን ለጎን በሀገሪቷና በህዝቧ ላይ ያንዣበበውን የተቀናጀ አፍራሽ የሚዲያ ዘገባ ለመመከት በጋራ መቆም እንዳለባቸው ምክር ቤቱ ያምናል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ  የመገናኛ ብዙሃን ሀገራችን የገባችበትን ጦርነት በተመለከተ እያሰራጩት ያሉት ዘገባ  ከተጨባጩ እውነታ ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን ከትክክለኛ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ጋር የሚጋጭ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በተለይም አንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አዲስ አበባና ዙሪያዋን እንዲሁም  በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ እያሰራጩት ያለው ዘገባ ህዝብን የሚያሸብርና ስጋት ላይ የሚጥል  ከመሆኑም በላይ ከተማዋን የጦርነት ቀጠና አድርጎ የማቅረብ ዝንባሌ እንዳለባቸው ታዝበናል፤ የከተማው ህብረተሰብ ግን እንደወትሮው ሁሉ የዕለት ተዕለት ተግባሩን ያለምንም መስተጓጎል እያከናወነ ይገኛል፡፡

መገናኛ ብዙሃን በጦርነት ጊዜም ቢሆን በህዝብ ላይ ተጨማሪ ጉዳት በማይደርስ መልኩ ከወገናዊነት ነፃ ሆነው መረጃን ለህብረተሰቡ ማቅረብ ያለባቸው ቢሆንም እነዚህ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ግን በጋዜጠኝነት ሙያ የማይፈቀድ ኢ ሚዛናዊ ዘገባን በስፋት እያሰራጩ  ነው፡፡ በመሆኑም  ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያካሄዱ ያሉትን የተዛባ ዘገባ ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ በመሆኑ ሊታረም ይገባል እንላለን፤

ፈቃድ አግኝተው በሀገር ውስጥ የሚሰሩ የውጭ ሀገር ወኪል ጋዜጠኞች ወቅቱ ከምንም ጊዜ በላይ ፈጣን እና ተዓማኒ መረጃ ማቅረብ የሚያስፈለግበት ወቅት ላይ ያለን መሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር መስራት የሚቻለው ሀገር ስትኖር መሆኑን በመገንዘብ የህዝቡን አብሮ የመኖር ባህልና ትውፊት የሚሸረሽር እንዲሁም ስጋት ላይ የሚጥል ዘገባ እንዳይተላለፍ ከፍ ያለ ጥንቃቄ ማድረግ  ይገባቸዋል፡፡

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም በአለም አለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ያልተረጋገጡና ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ዘገባዎችን እንዳለ ወስዶ ከማስተላለፍ በመቆጠብ የህዝብና ሀገር ውግናናቸውን እንዲሁም ለሙያቸው ያላቸውን ታማኝነት በተግባር ሊያሳዩ ይገባል፤ በተለይም ለዘመናት አብሮ በኖረው ህዝብ መሀል የሚሰራጩ  የጥላቻ ንግግሮችን ደግሞ ባለማሰራጨት  ህብረተሰቡን ማንቃት እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ ማስጨበጥ  ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ተቋማት ብዙ ይጠበቃል፡፡

በመጨረሻም መንግስት ተገቢውን ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ ከማድረስ አንፃር ተከታታይ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ በሚዲያዎች በኩል የማቅረብ ፍጥነቱን እንዲያሻሽል እያሳሰብን፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም ሀገርን ከብተና ለማዳን አደጋውንና  ስጋቱን በሚመጥን ደረጃ የተረጋገጡ መረጃዎችን በየዕለቱ በተቀናጀ ስልት በማቅረብ ግንዛቤ የመፍጠር ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል እንላለን፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ህዳር 25 ቀን 2014 አዲስ አበባ፤

 

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe