ዜናባለሥልጣኑ በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን በሚመለከት ሀገራዊ ሪፖርት...

ባለሥልጣኑ በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን በሚመለከት ሀገራዊ ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን በሚመለከት በጥናት ላይ ተመስርቶ ያዘጋጀውን ሪፖርት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የባለሥልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀፅ 8/4 ላይ ለባለሥልጣኑ የተሰጠውን ኃለፊነት መሰረት በማድረግ ሪፖርቱ እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡
ሪፖርቱ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በአምስት የማህበራዊ ሚድያ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማለትም በፌስቡክ፣ በቴሌግራም፣ በዩቱዩብ፣ በትዊተር እና በቲክቶክ ከታህሳስ 23 /2014 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 23/ 2015 ዓ.ም ያለው ስርጭት ላይ ትኩረቱን እንዳደረገ በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሪፖርቱ በሸፈነው አንድ ዓመት ውስጥ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ የዜጎችንና የሀገርን ሁለንተናዊ ደህንነትና ሰላም በሚያናጋ እና በሚያሳስብ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት አቅራቢዎችን በተመለከተም ዳሰሳ የተደረገባቸው የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎች ተጠቃሚዎችን ለጥቃት የሚያጋልጡ ይዘቶችን ከአገልግሎት አውታራቸው ላይ ለማስወገድ እና ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል በሚያስቀምጡት የማህበረሰብ ጥበቃ ህግና ደንብ መሰረት ተገቢ እርምጃዎችን አለመወሰዳቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በሪፖርቱ ላይ ማሕበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎችን ግንኙነትና አስተዳደርን የሚገዛ የህግና የፖሊሲማዕቀፍ ማውጣት፣ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ ማሳደግና የመፍትሄው አካል ማድረግ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከጥላቻ ንግግርና ከሐሰተኛ መረጃ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ጉዳት የሚደርስባቸውን ዜጎች ታሳቢ ያደረገ የህግ ተጠያቂነት ማስፈን እንደሚያስፈልግ በምክረ-ሃሳብነት ተመላክቷል፡፡
በመጨረሻም በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በቀረበው ሪፖርት እና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ገንቢና አዎንታዊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በውይይቱ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከመድረኩ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe