ዜናበጋዜጠኞች ላይ ጥቃት ከሚያደርሱ ከአስሩ ስምንቱ አይጠየቁም ተባለ

በጋዜጠኞች ላይ ጥቃት ከሚያደርሱ ከአስሩ ስምንቱ አይጠየቁም ተባለ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃ ሰራተኞች መረጃ ለህዝብ የማድረስ ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት በሚደርስባቸው ጥቃትና ግድያ ሳቢያ ተጠያቂ የሚሆኑት ከአስሩ ሁለቱ ብቻ መሆናቸው ተገለፀ፡፡

ይህ የተለገለፀው  በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ አማካይነት በየዓመቱ ጥቅምት 23 ወይም ኖቬምበር 2 የሚከበረው በጋዜጠኞች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስቆምና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በሚታሰብበት ዕለት በተዘጋጀ ሴሚናር ላይ ነው፡፡

በዩኔስኮ የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ እና በኬኒያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ትብብር  ናይሮቢ ግራንድ ፕላዛ ሆቴል በተካሄደው በዚህ አውደ ጥናት ላይ እንደተገለፀው ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ስራቸውን በነፃነት ለማከናወን የሚያስችላቸው አውድ በመንግስት አስፈፃሚ አካላት፤ በፖሊሶችና ፀጥታ አስከባሪዎች እንዲሁምን በህብረተሰቡ የሚደርስባቸው ጫና እየተባባሰ ከመምጣቱም በላይ ጥቃት አድራሾች ላይ የሚወሰድ ህጋዊ እርምጃ ባለመኖሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ስራቸውን አስቸጋሪ ማድረጉ ተብራርቷል፡፡

UNESCO Director Professoror
UNESCO Director Professor Hubert

በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የዩኔስኮ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሃበርት ጊዚኒ እንደተናገሩት በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀሙ እስከ ሞት የሚያደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ወንጀለኞችን ለፍትህ ለማቅረብ መንግስታት ጠንክረው ሊሰሩ አይገባል ብለዋል፡፡ ያለፉት ዓመታት ልምዳችን የሚያሳየን  ጋዜጠኞች በስጋት ላይ ሆነው ስራቸውን ማከናወናቸው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጋዜጠኞች ላይ ጥቃት ከሚያደርሱት አስር ሰዎች መሀከል ተጠያቂ የሚሆኑት ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን ይህም ሂደቱ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያመጣ ነው ብለዋል፡፡

ጋዜጠኞች ከስራቸው ጋር የተገናኘውን ጥቃት ለማስቆም በተለያዩ አካላት የተጀመሩት የመከላካል ስራዎች ውጤታማ እስከሚሆኑ ድረስ ጋዜጠኞች ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ካደረገ ግጭት ቀስቃሽ ዘገባ ራሳቸውን ማራቅ አለባቸው ያሉት የኬኒያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሚኒስትር ኑርዲኒ ሀጂ ልዩነት ላይ ያተኮሩ ዘገባዎች ለጠቅላላው ህዝብ ጥቅም ሲባል መወገድ ይኖርባቸዋል፤ ጋዜጠኞች ስነ ምግባር አክብረው መስራታቸው ለጥያቄ መቅረብ  እንደሌለበት አመልክተዋል፡፡

KMC Chairperson Mr. Maina Muiruri
KMC Chairperson Mr. Maina Muiruri

የኬኒያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሊቀ መንበር ሚስተር ማኒያ ሙዙሪ በበኩላቸው  በአፍሪካ ከምርጫና ከእርስ በእርስ ግጭት ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን የሚያጡ ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ጠቅሰው ባለፉት 10 ዓመታት  በሶማሊያ ብቻ 58 ጋዜጠኞች በስራ ላይ እያሉ የተገደሉ ሲሆን የግድያው ፈፃሚዎች አልተጠየቁም ብለዋል፡፡ በኬኒያም በርካታ የጥቃት ሰለባ ጋዜጠኞች መኖራቸውን ጠቅሰው በዚህም የተነሳ ጋዜጠኞች በስራ ላይ እያሉ የሚደርስባቸውን ጥቃት ለፀጥታ ሃይሎች ሲያመለክቱም ሆነ በፀጥታ ሰራተኞች  በራሳቸው የተያዙ የምርምራ ስራዎች ውጤታማነታቸው አነስተኛ ነው ብለዋል፤

በዕለቱ በተካሄደው የፖናል ውይይት ላይ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማለትም ከኬኒያ ፤ኢትዮጵያ፤ ኡጋንዳ፤ ሶማሊያ፤ ሩዋንዳና ከደቡብ ሱዳን የመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ውይይት አድርገዋል፡፡

ጋዜጠኞችን ከጥቃት ለመጠበቅና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ መወሰድ ባሉባቸው ስልቶች ላይ በተነጋገረው የፓናል ውይይት ላይ የተካፈሉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ታምራት ኃይሉ  የሀገራቸውን ልምድ ባካፈሉበት በዚህ መድረክ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት እንደሆነው ጠቅሰው በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚዲያ ባለሙያዎች ፈታኝ ጊዜ ማሳለፋቸውን ገልፀዋል፡፡ ከጦርነቱና ከምዕራብ ኢትዮጵያ ፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ያለፉ ሶስት ጋዜጠኞች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ታምራት የጥቃቱ ፈፃሚዎችም ሆኑ ማንነታቸው እስካሁን ድረስ በምርምራ አለመታወቁ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡

በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለማስቆምና በአጥፊዎች ላይም የህግ ተጠያቂነት ለማምጣት ከመንግስታት ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትና የመብት ተከራካሪዎች ቢያንስ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ግንኙነት በመፍጠር ተጠያቂነትን ለማምጣት በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል አቶ ታምራት፡፡

 Judie Kaberi
Judie Kaberi

በስራ ላይ ባሉ ሴት ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት በተመለከተ በተካሄደው የፖናል ውይይት ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩት የኬኒያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር ዳይሬክተር ጁዲ ካማራ እንደተናገሩት ሴቶች በተለያየ መልኩ የሚደርስባውን ጥቃት በመስጋት ጠንከር ያሉ የምርምራ ስራዎች ላይ የመሰማራት ፍላጎት እንደሚያጡ በመግልፅ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አስፈላጊ የሆኑ ከጥቃት መከላካያ መሳሪያዎችንና መረጃዎችን በመስጠት አጥቂዎችን እንዲያጋልጡ ሊያበረታቷቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የአርቲክል 19 የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚስትር ሙጉምቢ ኬታ በበኩላቸው የሚዲያ ተቋማት የጥቃት አድራሾችን ማንነት በዝርዝር ከመዘገብ ባለፈ ሪፖርት ማውጣት እንዳለባቸው በመጠቆም ለመብት ተከራካሪዎች የተጨበጡ ጥናቶችን ሊያቀርቡ እንደሚገባል አመልክተዋል፡፡

በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆምና አጥፊዎች አለመጠየቃቸውን ለማስቆም  በየዓመቱ ኖቬምበር 2 ወይም ጥቅምት 23 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ / አማካይነት እንዲከበር በተወሰነው መሠረት እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ መከበር የጀመረ ሲሆን መነሻውም ሁለት የፈረንሳይ ጋዜጠኞች በማሊ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ በስራ ላይ እያሉ  በመገደላቸው ሳቢያ ነው፡፡

1 COMMENT

  1. በቅድሚያ የዜናውን አዘጋጅ እናመሰግናለን ።ጋዜጠኝነት በጣም ፈታኝ ግን ደግሞ ለሀቅ በጽናት ማቆምን የሚጠየቅ ሞያ ነው።ጋዜጠኞች የተለያዩ ልዩነቶቻችንን ትተን ለሙያው መርሆዎች በጋራ መቆም አለብን ።ጋዜጠኝነት ከአክቲቪስትነት ፈጽሞ መለየት ይኖርበታል።ዩኔስኮ ይህን መድረክ ማዘጋጀቱ ተገቢ ቢሆንም ጋዜጠኞችን ለአደጋ በሚያጋልጡ ወገኖች ላይ ድምፁን በግልፅ ማሰማት ይጠበቅበታል ።ሴሚናር በማዘጋጀት ብቻ መታጠር የለበትም ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe