- የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች አያያዝ መክፋቱ ተጠቁሟል
ፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ለመንግሥት አመራሮች መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ሚናን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑ ተነገረ፡፡ የፀጥታ አካላትን ያቀፈ የምክክር ፎረም በመመሥረት በጋዜጠኞችና ሚዲያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቅረፍ መታቀዱም ተነግሯል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ካውንስል ጋር በመተባበር ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ባዘጋጁት የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን መታሰቢያ መድረክ፣ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚዲያዎችና ባለሙያዎቻቸው ላይ የሚደርሰው ጫና መባባሱ ተነግሯል፡፡ ይህን አሳሳቢ ሁኔታ ለማሻሻል ደግሞ የመንግሥት መዋቅሩን በተለይ የፀጥታ አካላትን ባቀፈ መንገድ ስለጋዜጠኝነት ሚና ግንዛቤ ከመስጠት ጀምሮ የምክክር ፎረም እንደሚመሠረት ተነግሯል፡፡
በኢትዮጵያ የዩኒስኮ የኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አደራው ገነቱ፣ የፀጥታ አካላትን ያቀፈ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ለመመሥረት ጥረት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በመደበኛነት ዩኒስኮ ስለጋዜጠኝነትና ሚዲያ ሚና ለፀጥታ አካላት ሥልጠና እንደሚሰጥ ያወሱት አቶ አደራው ‹‹ጥረታችን ከተሳካ በዚህ ዓመት ማጠናቀቂያ ወይም ብዙ ሳይርቅ የሕግ አካላትን ያቀፈ አገር አቀፍ የምክክር ፎረም እንመሠርታለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ አካላትና የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትን ያሳተፈ ሥራ የጋዜጠኞችን ነፃነት ለማስከበር ትልቅ ዕገዛ ይኖረዋል የሚል እምነት ዩኒስኮ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
አቶ አደራው አክለውም የመንግሥት አካላት ጋዜጠኞችንም ሆነ ሚዲያዎችን በጠላትነት ሊፈርጁ የሚችሉትና ከመረጃ ማግኘት ጀምሮ ዘርፉ ጫና የሚደርስበት በግንዛቤ አለመስፋት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሚዲያውና ጋዜጠኞች ችግር ሲገጥማቸው ተከታትሎ ለመፍታትም ሆነ የዘርፉን ነፃነት ለመጠበቅ ከመንግሥት በተለይ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ አዋጪ አማራጭ መሆኑን አቶ አደራው አስረድተዋል፡፡
የዘንድሮው የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን ለ31ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሰኞ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ታስቦ ሲውል የተለያዩ ጥናቶችና መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡ በዕለቱ መልዕክት ካስተላለፉት መካከል የዩኒስኮ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተሯ ዩሚኮ ዮኮዛኪ በሙያ የተገራ ጋዜጠኝነት፣ እውነተኛና ትክክለኛ መረጃ የሚያቀርብ ሚዲያ መኖር ከአገር አልፎ ለዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት ግብ መሳካት ጠቃሚ ነው ብለውታል፡፡ የውሸት መረጃና የተዛባ መረጃ ሥርጭት በሰፋበት ዓለም ‹‹ጋዜጠኝነትን በሙያ ከማነፅ በተጨማሪ ዘርፉ ገንቢ ሚና እንዲጫወት የሚያስችሉ የቁጥጥር ዕርምጃዎችም ያስፈልገዋል፤›› በማለት ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ፕሬዚዳንት አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው፣ የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት በኢትዮጵያ የፈጠረውን ተፅዕኖና አገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታን ትኩረት በማድረግ የሚዲያ ሚና ምን መሆን እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ዲጂታል ሚዲያው ሁለት ዓይነት ገጽታ ያለው ነው፡፡ አንዱ ፈጠራ የበዛበትና ሀቅ የማይረጋገጥበት፣ የግጭት መረጃ የሚሠራጭበት ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ሙያዊ ሥነ ምግባርና ኃላፊነቱን ጠብቆ የሚሠራ ነው፤›› በማለት አቶ አማረ የዲጂታል ሚዲያውን ገጽታ አስቀምጠዋል፡፡ አሁን ላይ በአክቲቪዝምና በጆርናሊዝም መካከል የሚና መደበላለቅ እንደሚታይ ያመለከቱት አቶ አማረ፣ ግጭት መጠላላትና የውሸት መረጃ ሥርጭት ቆሞ ዘርፉን ገንቢ ለሆነ ሚና ለማዋል መሥራት እንደሚኖርበት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
በዚሁ የዓለም ፕሬስ ቀን መታሰቢያ ዝግጅት ላይ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ የዲጂታል ሚዲያ ማደግና መስፋፋት ያለውን ፈተናና በጎ ዕድል የዳሰሱ የውይይት ሐሳቦችም ቀርበዋል፡፡ የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት ሜን ስትሪም በሚባለው መደበኛው የሚዲያ ዘርፍ ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ የገመገሙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ቤት መምህር ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) ዘርፉ በፖለቲካ፣ በስሜት፣ በጥላቻ፣ በወገንተኝነትና በሐሰት መረጃ ፍብረካ ተፅዕኖ ውስጥ መውደቁን አመልክተዋል፡፡ የተሳሳተ መረጃ ሥርጭት፣ ግጭት ቅስቀሳና ጥላቻ ማስፋፋት ቀላል በሆነበት በዚህ በዲጂታል ሚዲያ አብዮት ግጭትና ቀውስ ውስጥ ያሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ዘርፉን በጥንቃቄ መያዝ እንደሚገባቸው ባለሙያው መክረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ጋዜጠኛ አበኒዮም ሲሳይ በበኩላቸው የዲጂታል ሚዲያ ዕድገት የፈጠረውን ዕድል ለማመላከት የሚሞክር ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ዲጂታል ሚዲያው መደበኛው ሚዲያዎች በተናጠል የያዙትን ቅርፅና አቀራረብ በሙሉ በአንድ አካቶ የያዘ ለአጠቃቀምም የቀለለ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አበንዮም፣ በአሁኑ ወቅት ስለ ቴክኖሎጂው ያለንን ዕውቀት ማሳደግና ከመደበኛው ሚዲያ ጋር ቀይጦ ዘርፉን መጠቀም አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡ መደበኛ ሚዲያዎች ተለዋዋጭና ከዘመኑ ጋር የሚሄድ ሁኔታን በመፍጠር ዲጂታል ሚዲያውን በሰፊው በመጠቀም ዘርፉን መግራትና ለበጎ ሚና ማዋል እንደሚችሉም አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት የሴቶች ውክልናና ሚና ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ የገመገሙት ከኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማኅበር ጋዜጠኛ ቤቴልሔም ነጋሽ በበኩላቸው፣ ከዘርፉ ሴቶች ያገኙትን ዕድልና የገጠማቸውን ፈተና አቅርበዋል፡፡ የሴቶች መብት ተነካ ሲባል ወይም የሴቶች ማኅበራዊ ጉዳት ሲነገር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ቅስቀሳ በማድረግ ለውጥ ያመጡ በጎ ዘመቻዎች መካሄዳቸውን ጋዜጠኛ ቤቴልሔም አሳይተዋል፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች ላይ ተፅዕኖና መድሎ አልፎ ተርፎም ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃት ለመፈጸም ዲጂታል ሚዲያው እየዋለ እንደሚገኝ በማሳያ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡ በዚህ ረገድ የዘርፉን ጉዳት በመቀነስ የሴቶችን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመቅረፍ በሚረዳ መንገድ ሚዲያውን መጠቀም እንደሚቻል ነው ባለሙያዋ ምክራቸውን የሰጡት፡፡
ስለሚዲያ ተጠያቂነትና ተዓማኒነት የውይይት ሐሳብ ያቀረቡት ከኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ሥራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ በበኩላቸው ልክ እንደመደበኛው ሚዲያ ሁሉ ዲጂታል ሚዲያውንም ክትትል በማድረግ በዘርፉ ተጠያቂነትና ተዓማኒነት መገንባት እንደሚቻል ለማመልከት ሞክረዋል፡፡ አሁን ላይ የሚዲያ ሰዎችና ሚዲያዎች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችና እስራቶች ከሁሉ በላይ አሳሳቢ እየሆኑ እንደመጡ ያመለከቱት ጋዜጠኛ ታምራት ‹‹መንግሥት አንድ ዕርምጃ ሲወስድ ለምን ተብሎ ካልተጠየቀ በስተቀር ተደጋጋሚ ስህተቶችን መፈጸሙን ይቀጥላል›› ብለዋል፡፡ በጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እስራት ወቅት መንግሥት ለምን ቢባል ኖሮ የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እስራትና መሰወር ላይደገም ይችል እንደነበር ያስረዱት ጋዜጠኛ ታምራት፣ ነገር ግን ይህን የሚያደርግ ባለመኖሩ መንግሥት በጥፋቱ እንደገፋበት አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ እንደተስተጋባው ከሆነ የጋዜጠኞች መታሰርና ያሉበት ሁኔታ ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ መሰወር እጅግ አሳሳቢ ችግር መሆኑ ተነስቷል፡፡ ጋዜጠኞችም ሆኑ ሚዲያዎች ሥራቸውን ሲሠሩ ተጠያቂነትና ተዓማኒነት ባለው መንገድ ሙያውን እንዲተገብሩ እንደሚጠበቅባቸው ሁሉ፣ መንግሥትም የአገሪቱን ሕግ ተከትሎ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንደሚጠበቅበት በመድረኩ ተነስቷል፡፡ የዲጂታል ሚዲያውን በመጠቀም ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ ንግግሮች በማሠራጨት ሊወቀስ የሚገባው ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ከባድ የሕግና የሥነ ምግባር ኃላፊነት ያለባቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተቋማት ጭምር መሆናቸው እንደ ትልቅ ችግር ተጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ ለውጡ እንደመጣ ወደ ሥልጣን የመጣው መንግሥት ብዙ የሚዲያ ዘርፍን የጠቀሙ ዕርምጃዎች መውሰዱንና የሕግ ማሻሻያዎችን ጭምር ማድረጉ በበጎነት ተወስቷል፡፡ አገሪቱ በዓለም ስሟ እንዲጠቀስ ያደረገ የፕሬስ ነፃነት ሪኮርድ መሻሻል መታየቱ በሚበረታታ መንገድ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዘርፉ ይዞታ ማሽቆልቆል እየታየበት ነው ተብሏል፡፡
በተደጋጋሚ የሚታዩ የጋዜጠኞች እስራቶች፣ መረጃ በቀላሉ ማግኘት አለመቻል፣ በሁሉም ቦታ ተንቀሳቅሶ እንደልብ መዘገብ አለመቻል፣ የዘርና የሃይማኖት ቁርሾዎች፣ ግጭትና ጦርነቶች እንዲሁም የፖለቲካ ልዩነትና ፅንፈኛ አመለካከቶችን ጨምሮ ሌሎችም ችግሮች የዘርፉ ይዞታ ማሽቆልቆል ማሳያ ተብለው በመድረኩ ቀርበዋል፡፡