ወቅታዊ መግለጫበኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ እየደረሰ ላለው ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ...

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ እየደረሰ ላለው ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ  ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ ስለመጠየቅ

ግንቦት 10 / 2012 ዓ.ም

ለ፡   ክቡር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ

     የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

     አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡-      በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ እየደረሰ ላለው ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ  ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ ስለመጠየቅ

የኢትዮጵያ መገናኛ  ብዙሃን   ምክር  ቤት   በሥነ  ምግባር   የታነፀ     በሃላፊነት  ስሜት  ህዝብን  የሚያገለግል ሚዲያ  በሀገራችን  እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ የህዝቦች  ስጋት የሆነው  የኮሮና  ቫይረስ  እያደረሰ  ያለውን ተጽእኖ ለመመከት  ህዝብና መንግስት እያደረጉ ያሉትን ርብርብ በአድናቆት  ይመለከታል፡፡

ምክር ቤቱ  በመገናኛ ብዙሃን ስራ ላይ የተሰማሩ ልዩ ልዩ አካላትን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች የዘርፍ ማህበር፤ የማህበረሰብ ራዲዮ ማህበር፤ ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበርንና በተለያየ መልኩ የተደራጁ  የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን አቅፏል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን መከሰቱ በመንግስት ከተገለፀበት ቀን ጀምሮ መገናኛ ብዙሃን  ለጉዳዩ ልዩ ትኩረትን  በመስጠት ህብረተሰቡ ለበሽታዉ ያለዉን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ ከመንግስት የሚወጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ብሎም ዕለታዊ መረጃዎችን ለህዝቡ በማድረስ እያደረጉ ያለዉ አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መምጣት ጋር ተያያዞ ዘርፈ ብዙ  ችግሮችን በየተቋሞቻቸው እያስተናገዱ ነው፡፡ ሚዲያዎች በሙሉ አቅማቸው መረጃን ማስተላልፍ አለመቻላቸው የችግሩ ስፋት ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት ወጥቶ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል ሊፈጥር ይችላል፡፡

በመሆኑም ይህንኑ መሠረት በማድረስ በቅርቡ ኮቪድ 19  በመገናኛ ብዙሃን ስራ  ላይ ስላለው ተፅእኖ ለመወያየት የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ተከታታይ የቪዲዮ ውይይት በምክር ቤታችን አስተባባሪነት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ የህዝብና የንግድ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የማህበረሰብ  ሚዲያዎች ፣ የጋዜጠኞች ማህበራት ፣ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተወካዮች ፣ ተደማጭነት ያላቸው አርታኢዎች ፣ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ልማት ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን ተሳታፊዎቹ የሚዲያ ኢንዱስትሪውን ፈታኝ ሁኔታዎች ለይተው በመወያየት በጋራ  አንድ መፍትሔ  ለመፈለግ የጥናት ሰነድ አዘጋጅተዋል፡፡

ሚዲያዎቹ የተጋረጠባቸዉ የገንዘብ እጥረት የከፋ በመሆኑ የተከበረዉ ቢሮዎን ለማሳወቅና አስፈላጊዉ ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ በታላቅ አክብሮትና ትህትና ይህንን የጥናት ሰነድ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አባሪ አድርገን አቅርበናል፡፡

ክብርነትዎ  ምክር ቤታችን  አባላቱን ወክሎ ያቀረበዉን ጥያቄ ተመልክቶ ተገቢዉን አፋጣኝ ምላሽ  እንደሚሰጥ ፅኑ እምነት አለን፡፡ ይህ ወረርሽኝ በሀገራችን የከፋ ችግር እንዳያስከትል ሕብረተሰቡን በማንቃትና ጥንቃቄዉን ይበልጥ እንዲያጠናክር ከዚህ ቀደም ስናደርግ እንደነበረዉ ሁሉ አበክረን የምንሰራ መሆናችንን ልንገልፅልዎ እንወዳለን፡፡

ለሚደርግልን ቀና ትብብር ሁሉ በቅድሚያ እናመሰግናለን!

 

ከሠላምታ ጋር!

አማረ አረጋዊ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ

ግልባጭ፡-

– ለሠላም ሚኒስቴር

– ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe