ወቅታዊ መግለጫ‹በኢንተርኔት ግንኙነት ላይ የተጣለው ገደብ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በአግባቡ ለህዝብ ተደራሽ እንዳያደርጉ...

‹በኢንተርኔት ግንኙነት ላይ የተጣለው ገደብ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በአግባቡ ለህዝብ ተደራሽ እንዳያደርጉ እንቅፋት በመሆኑ ገደቡ ሊነሳ ይገባል›

ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/

(የካቲት 242015 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት  በአንዳንድ የኢንተርኔት የግንኙነት መተግበሪያዎች ላይ የጣለው ገደብ መገናኛ ብዙሃን በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን መረጃ የማሰባሰብ፤የማደራጀትና ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ መብት ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ተገንዝበናል፤ በተለይም የሰበሰቡትን መረጃ በሀገርና በውጭ ሀገር ለሚገኙ ተደራሲያን ኢንተርኔትን እንደ ዋነኛ የመረጃ ማሰራጫ የሚጠቀሙ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በአግባቡ ለመከወን መቸገራቸውን ለምክር ቤታችን የደረሱ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አቤቱታ ያሳያል፤

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238 ላይ  በግልፅ እንደተመለከተው የበይነ መረብ ጋዜጠኞችና ፈቃድ ያለው ማንኛውም የሚዲያ ተቋም ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት እስካገኘ ድረስ በመደበኛው መገናኛ ብዙሃን እና በበይነ መረብ  የሚተገበሩ የአገልግሎት  መድረክ ወይም ፎርማት  (ድረ ገፅ፤ዩ ቲዩብ፤ ፌስ ቡክ፤ቲውተር፤ኢንታግራም፤ሊንክዲን ወዘተ)ሁሉንም ሙያዊ ስነ-ምግባር እና የጋዜጠኝነት ዋና እሴቶችን እስካከበሩ ድረስ ገደብ ሊጣልባቸው አይገባም፤

በመሆኑም ሰሞኑን  በሀገራችን ከተፈጠረው ኃይማኖታዊ አለመግባባቶች ጋር በተያያዘ  የችግሩን ስፋትና ክብደት ከግምት በማስገባት  ሊቀለበስ የማይችል አደጋን ምክንያት በማድረግ ካልሆነ በስተቀር ሕግን መሰረት በማድረግ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ መንግስት ገደብ ሊያደርግ  እንደማይገባ እናምናለን፤  ከዚህ አንፃር በአንዳንድ የኢንትርኔት መረጃ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች ላይ የተጣለው ገደብ ሶስት ሳምንታትን ያስቆጠረ ከመሆኑም በላይ ገደቡ የተደረገበትን ምክንያት የሚመለከተው መንግስታዊ አካል የሰጠው ግልጽ  ማብራሪያ የለም፤ የተፈጠሩ ክስተቶችን ከህግ ውጭ ሊያባብሱና ግጭት ለመቀስቀስ  የሚጥሩ አንዳንድ የበይነ መረብ መገናኛ  ብዙሃንን  እንኳ በህግ አግባብ ተጠያቂ ከማድረግ በዘለለ የጠቅላላ ህዝቡን መረጃ የማግኘትና የማሰራጨት መብት ላይ ገደብ ለመጣል የሚያበቃ አማራጭ እንዳልሆነ ምክር ቤታችን ያምናል፤

በተለይም ለዓመታት ለህብረተሰቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ ሆኖ የዘለቀው የህትመት መገናኛ ብዙሃን ከወረቀት ዋጋ መናርና ከህትመት መወደድ ጋር በተያያዘ ከገበያ ውጭ በሆኑበት በዚህ ወቅት ኢንተርኔትን አማራጭ የመረጃ ማስተላላፊ መንገድ አድርገው አገልግሎት እየሰጡ ባሉ የሚዲያ ተቋማት ላይ የፈጠረው ተፅእኖ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት በኢንትርኔት ግንኙነት ላይ የጣለው ገደብ መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በአግባቡ ለህዝብ ተደራሽ እንዳያደርጉ እንቅፋት በመሆኑ ገደቡ ሊነሳ ይገባል እንላለን፡፡

በሌላ በኩል ማንኛውም መደበኛም ሆነ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩአቸው መረጃዎች በህብረተሰቡ መሀከል  የእርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳት፣ የሌሎችን መብት ወይም እምነት ማንኳሰስ፣ ወይም በሃይማኖት ተከታዮች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀሰቀስ እንደማይፈቀድ የተደነገገ በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውንም መረጃ  በሚያሰራጩበት ወቅት በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በሃላፊነት መንፈስ እንዲሁም ከፍ ባለ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር በመመራት  ሊሆን እንደሚገባ በአፅንኦት እናሳስባለን፡፡

 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

የካቲት 24 ቀን 2015 አዲስ አበባ፤

 

 

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe