Uncategorized‹‹ በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ የሚፈፀም ዘረፋና የወንጀል ድርጊት መደጋገም ሃሳብን በነፃነት...

‹‹ በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ የሚፈፀም ዘረፋና የወንጀል ድርጊት መደጋገም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ መብት ላይ ስጋት ደቅኗል››

ጋዜጣዊ መግለጫ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/

(ነሐሴ 142015 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፤

ምክር ቤታችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ የቢሮ ዘረፋ እንደተፈፀመባቸውና በዚህም ሳቢያ ተቋማቱ የእለት ተዕለት ስራዎቻቸውን ለመስራት ባለመቻላቸው ጋዜጠኞች ስራቸውን ለማቆም መገደዳቸውን ተገንዝቧል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 4 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው ‹ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፤ሃሳቦች፤አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው በሕግ ጥበቃ ይደረግለታል› ይላል፡፡ ሆኖም ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ጥበቃ ለማድረግ የወጡ የሕግ ድንጋጌዎች ቢኖሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገሪቱ ህግ መሠረት ተመዝግበውና ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ባልታወቁ ግለሰቦች ቢሮአቸው እየተዘረፈና መረጃ ለመቀበልና ለማስተላላፍ የሚጠቀሙባቸው መሳሪዎችም እየተወሰዱባቸው መሆኑን ምክር ቤታችንን አሳስቦታል፡፡

የወንጀል ድርጊቶች ከመፈፀማቸው በፊት መከላከል ተፈፅሞ ሲገኝም አፋጣኝ ፍትሐዊ እርምጃዎችን በህግ አግባብ የመውሰድ ህገ መንግስታዊ ግዴታ የተጣለባቸው የፀጥታ አካላት ጋዜጠኞች መረጃ የመሰብሰብ የማደራጀትና ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ድጋፍ ከማድረግ ተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ላይ ስራቸውን የሚያስተጓጉል ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት እንዳይፈፀም ተገቢ የሆነ ጥበቃ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በአራት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት (በአራት ኪሎ ሚዲያ፤በ251 ሚዲያና በየነታ ቲዩበ፤ አሁን ደግሞ በኢትዮጰያ ኢንሳይደር የበይነ መረብ ሚዲያ) ላይ የተከሰቱት ተደጋጋሚ የቢሮ ዘረፋዎች በወቅቱ ለሚመለከታቸው የፖሊስ አካላት ሪፖርት ቢደረግም በድርጊቱ ተሳታፊ በሆኑ ግለሰቦች ላይ የተያዘው የምርምራ ሂደት ምን እንደረሰ አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን የቢሮ ዘረፋው የቢሮ በር ሳይሰበር፤በእረፍት ቀናት፤ በተመረጡ ድርጅቶችና በሚዲያ ቁሳቁሶች ላይ መፈፀሙን ከተቀማቱ ሪፖርት ለመረዳት ችለናል፡፡ በመሆኑም የዘረፋው መደጋገም ድርጊቱ በተራ ግለሰቦች የተፈጸመ ነው ለማለት ጥርጣሬ የሚጭር ሆኗል፡፡ ድርጊቱ እንደተፈፀመም በተቻለ ፍጥነት ምርምራ በማድረግ አጥፊዎችን ህግ ፊት የማቅረብ ሂደቱ ዘገምተኛ መሆኑ በአዋጁ መሠረት  ጋዜጠኞች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ፤ እንዲሸማቀቁና የፕሬስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ እያደረገው ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገፀታ ላይ ጥላ የሚያጠላ ሆናል፡፡

የሕግ አስከባሪ አካላት በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ወንጀል ተፈፅሟል ብለው በሚያምኑበት ወቅት በአዋጁ ብቻ መመራት እንዳለባቸው ምክር ቤታችን በተደጋጋሚ መግለጫ ያወጣ ቢሆንም አሁን ባልታወቁ ሰዎች በተቀናጀና የተናበበ በሚመስል መልኩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ቢሮና መሳሪያዎች ላይ ተደጋጋሚ ዘረፋ መፈፀሙ ነገሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት የፀጥታ አካሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ያለ ቢሆንም ጋዜጠኞችንና ተቋማቱን በተመለከተ በሕጉ አግባብ ጥበቃ በማድረግ ህገወጥ ድርጊቶችን ለማስቀረት ያለመቻሉ ምክር ቤታችንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡

የሀገሪቱ ከፍተኛ የሕግ አውጭ አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ይበልጥ ለማስፋትና ሙያተኞች በሃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ለማበረታታት ያለመ ቢሆንም በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ የሚፈፀም ዘረፋና የወንጀል ድርጊት መደጋገም ከሕጉ መንፈስ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ዜጎች በመረጡት የመገናኛ ብዙሃን ሙያ ዘርፍ የመሰማራት፤ድርጅት የማቋቋምና መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ መብት ላይ ስጋት ደቅኗል፡፡

 

በመሆኑም መንግስት የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተገቢ የሆነ ጥበቃ በማድረግ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በሚያሰፋና የዜጎችን የዲሞክራሲያው ስርዓት ተሳትፎ በሚያጎለብት መልኩ ሊያከናውን ይገባል፤ ማናቸውም ሕግን የማስከበር ተግባራትም በሕግ አግባብ ብቻ መመራት ስላለበት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መሠረት እንዲኖረው የፍትሕ ሥርዓቱ በመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ላይ የተፈፀመውን የወንጀል ድርጊት በተቻለ ፍጥነት ተከታትሎ የምርመራውን ውጤት ለህዝብ ይፋ በማድረግ ሕገመንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የፍትሕ ስርዓቱ በሕግ በተደነገገው አሰራር እንዲመሩ ከማሳሰብ በተጨማሪ ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ጥንቃቄ እንዳይለያቸው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ነሐሴ 14 ቀን 2015 አዲስ አበባ፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe