ዜናበመላው ዓለም 293 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ሲፒጄ አስታወቀ

በመላው ዓለም 293 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ሲፒጄ አስታወቀ

በመላው ዓለም 293 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ሲፒጄ አስታወቀ; ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች በአውሮፓውያኑ በ2021 ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት የሁለተኝነት ደረጃን መያዟን አስታወቀ።

ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ) ዛሬ ይፋ ባደረገው ከሰሃራ በታች ጋዜጠኞችን በማሰር የቀዳሚነቱን ስፍራ ያያዘችው ኤርትራ መሆኗን አመልክቷል።

ሪፖርቱ ዘጠኝ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቅሶ ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ሁለተኛ እንዳደረጋትና ከጥቂት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ታይቶ የነበረው መሻሻል ወደኋላ ተመልሷል ብሏል።

ከሦስት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከ13 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት አገር መባሏ ይታወሳል። በወቅቱም የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በመዲናዋ አዲስ አበባ ተከብሮ ነበር።

“ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ትልቁ ወደ ኋላ መመለስ የታየው በኢትዮጵያ ነው። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከሰሃራ በታች ከኤርትራ ቀጥሎ ሁለተኛው በርካታ ጋዜጠኞችን ያሰረ ሆኗል” ሲሉ የሲፒጄ የኢዲቶሪያል ዳይሬክተር አርሌን ጌትስ ተናግረዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ክልል ባሉ አማጺያን መካከል በመደረግ ላይ ያለው ጦርነት ለበርካታ እስሮች ምክንያት መሆኑን ተገልጿል።

በዚህም መሠረት አሁን በኢትዮጵያ በእስር ላይ ካሉት ዘጠኝ ጋዜጠኞች ውስጥ ስድስቱ ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ የጦርነቱን መጋጋል እና እርሱን ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ የታሰሩ መሆናቸውን ዳይሬክተሯ በሪፖርታቸው ላይ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የጋዜጠኞችን አስር በተመለከተ በሲፒጄ በወጣው ሪፖርት ላይ አስካሁን ያለው ነገር የለም።

በአጠቃላይ የአፍሪካ አህጉር 25 ጋዜጠኞችን በማሰር ግብፅ ቀዳሚ ስትሆን፣ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ 9 ጋዜጠኞችን በማሰር ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የሲፒጄ ሪፖርት በተጨማሪም የኦሮሚያ ብሮድካስቲን ኔትወርክ ባልደረባ የነበረው ሲሳይ ፊዳ ላይ በደምቢ ዶሎ ከተማ ግድያ መፈጸሙንም ሪፖርቱ አስታውሷል።

ሲፒጄ ከዚህ ቀደም ባወጣው ሪፖርት ሲሳይ በሁለት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተተኩሶ መገደሉን እና የአካባቢው ባለሥጣናት ግድያውን የፈጸመው አባ ቶርቤ የተሰኘው ገዳይ ቡድን መሆኑን መግለጻቸውን ጨምሮ ማስነበቡ ይታወሳል።

በአጠቃላይ በዓመቱ 19 ጋዜጠኞች በመላው ዓለም መገደላቸውን እና ይህም ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው 22 ሞት የተወሰነ መቀነስ የታየበት መሆኑን ሪፖርቱ ተመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ሦስት ጋዜጠኞች ግጭት ባለበት አካባቢ ውስጥ ሲዘግቡ እንዲሁም ሁለት ጋዜጠኞች ደግሞ የአደባባይ አመጽ ሲዘግቡ መገደላቸውን ሲፒጄ አክሎ ገልጿል።

ሕንድ እና ሜክሲኮ በርካታ ጋዜጠኞች የተገደሉባቸው አገራትን ሰንጠረዥን በበላይነት ሲመሩ ቡርኪና ፋሶ፣ ሶማሊያ እና ኮሎምቢያም በዓመቱ በርካታ ጋዜጠኞች ከተገደሉባቸው አገራት መካከል ናቸው።

ቻይና ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በጋዜጠኞች እስር አንደኛ ሆነ የቆየች ሲሆን በተገባደደው የፈረንጆች ዓመትም 50 ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች። ሚያንማር፣ በግብፅ እና ቬትናምም ቻይናን ይከተላሉ።

ኢትዮጵያም በእስሩ ሰንጠረዥ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን በአጠቃላይ እስከ ኅዳር ወር መጀመሪያ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም 293 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ እና ከእነዚህ ውስጥም 14 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውን የሲፒጄ ሪፖርት አመላክቷል።

ይህም ተቋሙ መረጃው ማጠናቀር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑን፣ ብሎም አገራት አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሕጎችን ያወጡበት ዓመት መሆኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ምንጭBBC Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe