መቀመጫቸውን ሐገር ውስጥም ሆነ ከሐገር ውጭ ያደረጉና ስለ ኢትዮጵያ የሚዘግቡ የመገናኛ ብዙኃን ሙያዊ መርህን ካልተከተለ አዘጋገብ እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር አሳሰበ፡፡ ማኅበሩ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳለው ጋዜጠኞች ሚዛናዊ ያልሆኑና ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጠ ዘገባዎችን ከመስራት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ከፖለቲካዊ ውግንና ያልጸዱ እና ግጭት አባባሽ ዘገባዎችም ለሐገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ያልተገቡ ናቸው ብሏል፡፡
ማኅበሩ የተወሰኑ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በቅርቡ ስለአዲስ አበባ ከተማ የሰሯቸውን የተዛቡ ዘገባዎች ኮንኗል፡፡ ትክክለኛውን የጋዜጠኝነት መርህ ሳይከተሉ የተሰሩት ዘገባዎች የሐገር ሉአላዊነትን እና የሕዝቦችን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ስለመሆናቸውም አንስቷል፡፡ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሚድያዎች በሚሰሩ ጋዜጠኞች አባላቱ እና ከአካባቢው ነዋሪዎች እማኝነት በአዲስ አበባ ከተማ እና ዙርያዋን አስመልክቶ የተሰራጨው ዜና የሐሰት መሆኑን አረጋግጧል፡፡
በተጨማሪም የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን መረጃ ለጋዜጠኞች በመስጠት እውነተኛ መረጃን ለሕዝብ የማቅረብ ጥረቱን እንዲደግፉ ማኅበሩ በመግለጫው ጠይቋል፡፡