ዜናምክር ቤቱ መገናኛ ብዙሃን የአካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳሰበ

ምክር ቤቱ መገናኛ ብዙሃን የአካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- ጋዜጠኞች የአካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጥሪ ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከዩኔስኮ እና ፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የዓለም የፕሬስ ቀንን በማስመልከት “ጋዜጠኝነት በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ውስጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት አክብሯል።

በመርሀ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ የጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ ትዕግሥት ይልማ እንዳሉት፤ የሀገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡ የአካባቢያዊ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው ሊዘግቡ ይገባል።

መገናኛ ብዙሃን በአካባቢ ጥበቃ ላይ ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ሕጎችና አሠራሮች እንዲሁም ለአካባቢ ደህንነት ጠንቅ የሆኑ አመለካከቶች ላይ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ትኩረት እንዲያገኙ መጣር ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በአካባቢ ጥበቃ ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ሊደነቅ የሚገባው መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ትዕግሥት፤ የአካካቢ ጥበቃ ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ሁል ጊዜም ችላ ሊባል የማይገባው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ የአካባቢ ብክለት ስለሚያስከትለው ጉዳትና ስለመፍትሄዎቻቸው ሲዘግቡ ወቅታዊ መረጃና ሁሉን አቀፍ እሳቤን በሚያጎላ መንገድ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ጋዜጠኞች ከስጋትና ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ነፃ ሆነው እንዲሠሩ ሊመቻች ይገባል። ሰላማዊ ምህዳር እንዲኖር እንዲሁም ዜጎች ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙበት እሳቤ የሚጎላበት ቀን ሆኖ በዓሉ እንዲከበርም ያስፈልጋ ሲሉ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ትግስት እንዳመላከቱት፤ “ጋዜጠኝነት በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ውስጥ” የሚለው የፕሬስ ነፃነት መሪ ሃሳብ መገናኛ ብዙሃን በአካባቢያዊ ጉዳዮችም ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ጉዳዩን በትኩረት እንዲያዩ ያስችላቸዋል።

ምክር ቤቱም ስራቸውን ከስጋትና ፍርሃት ነፃ የሚሠሩበት ሁኔታ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ሰብሳቢዋ የዓለም አቀፉ የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር ጋዜጠኞች ስራቸውን ከስጋትና ፍርሃት ነፃ ሆነው በኃላፊነት ስሜት የሚሠሩበት ሁኔታ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ምክር ቤታቸው እምነቱ መሆኑን አስረድተዋል።

ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ዘገባዎች ሁሉን አቀፍ እሳቤ በሚጎላበት መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለሀገሪቷ ሰላም ሁሉም የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ላይ የመገናኛ ብዙሃን በተመለከተም ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፤ ከተለያዩ የሙያ ማኀበራት፣ ጋዜጠኞች፣ የዘርፉ ተዋንያን የተነሱ ሃሳብና ጥያቄዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

ዳግማዊት ግርማ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe