ዜናመገናኛ ብዙኃን ከጎሳና ከጠባብ ወገንተኝነት ተላቀው የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሊሠሩ እንደሚገባ...

መገናኛ ብዙኃን ከጎሳና ከጠባብ ወገንተኝነት ተላቀው የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከጎሳና ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት በመላቀቅ፣ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ባህልና ሳይንስ ማዕከል (ዩኔስኮ) አማካይነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የዓለም ፕሬስ ቀን ለ30ኛ ጊዜ ‹‹መረጃ ለሕዝብ ጥቅም›› በሚል መሪ ሐሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንና በሌሎች አካላት ትብብር ማክሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል በተከበረበት ወቅት ነው፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በወቅቱ እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ያለው የሚዲያዎች ቁጥርና በነፃነት የመሥራት እንቅስቃሴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ መሻሻል ቢያሳይም፣ በጎሳ ፍላጎትና በጠባብ የፖለቲካ ወገኝተኝነት ተገፍቶ ችግርን የማባባስ ዝንባሌ አሁንም የዘርፉ ችግሮች ናቸው፡፡

ከማኅበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የመረጃ መዛባት በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በሚዘረጉ አውታሮች በግለሰቦችና ቡድኖች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሠራጭ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ ድርጊት የአገርን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ከማወኩ በላይ በራሱ በፕሬስ ነፃነት ላይ ጭምር አደጋ እየጋበዘ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ለፓናል ውይይት መነሻ ጥናት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ሙላት ዓለማየሁ (ዶ/ር)፣ ላለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን አሠራሮችና ተግዳሮቶች ለፓናል ውይይት መነሻ ሐሳብ መልክ አቅርበዋል፡፡

ሙላት (ዶ/ር) እ.ኤ.አ. 1995 እስከ 1996 ያለው ጊዜ ብዙ መገናኛ ብዙኃንን ወደ ፊት ማምጣቱን ተከትሎ በጥሩ እንደሚነሳ አስታውሰው፣ ሆኖም የሙያዊ ዕድገትና ሥርዓትን አክብሮ ከመንቀሳቀስ አንፃር ክፍተቶች እንደነበሩት ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1996 እስከ 1999 ያለው ጊዜ በአንፃሩ በጥሩ እንደማይነሳና በርካታ ጋዜጦች የተዘጉበትና ጋዜጠኞችም እንዲሁ በብዙ ቁጥር የታሰሩበት እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2005 ተመልሶ ወደ ጥሩ እንቅስቃሴ የመጣ የሚዲያ ታሪክ እንደነበረ፣ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገሪቱ የሚዲያ ነፃነት ደረጃ ከ180ዎች ደረጃ ተሻሽሎ ወደ 112 ደርሶ እንደነበር አስታውቀው፣ ሆኖም ከምርጫ 97 በኋላ ጥሩ ሁኔታ እንዳልተፈጠረና ብዙ ጋዜጠኞችም የታሰሩበትና ከአገር የተሰደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ ያለው ጊዜ በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ጥሩ ዕድል ፈጥሯል ያሉት ሙላት (ዶ/ር)፣ ሆኖም በዚያው ልክ ታይተው የማይታወቁ ፈተናዎችም ታይተውበታል ብለዋል፡፡

አብዛኞቹ የመገናኛ ብዙኃን ያገኟቸውን መረጃዎች እርስ በእርስ የመጋራት ልምዳቸው ዝቅተኛ ነው ያሉት ሙላት (ዶ/ር)፣ ተባብሮ ከመሥራት ይልቅ ወደ ፉክክር የሚሄዱበት መንገድ እንደሚያደላ፣ ሆኖም ያንን ማስተካከል ከተቻለ የአገሪቱ ሚዲያዎች ለኅብረተሰቡ የተሻለ ነገር እንደሚያበረክቱና በሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚዛመተውን የሐሰት መረጃ መከላከል እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የሥራ አስፋጻሚ አባል አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው፣ ‹‹መረጃ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል በፕሬስ ነፃነት ላይ ድርድር አይኖርም ማለታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡ መረጃ የሚተላለፈው በዘፈቀደ ሳይሆን የሥነ ምግባር መርህን ተከተሎ ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ አማረ፣ በዚህ ወቅት ለፕሬሶች የሥነ ምግባር መርህን የያዘ መረጃ ለኅብረተሰቡ በአግባቡ ባለመሰጠቱ ሕዝቡ በትክክለኛው መንገድ ለአገር ግንባታ፣ ለሰላም፣ ለልማት ከመሳተፍ ይልቅ ሚዲያው በሚሰጠው የተሳሳተ መረጃ ወደ ግጭት፣ መራራቅ፣ ይህንንም ተከትሎ ወደ ሰላም ዕጦት እየሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከመረጃ ነፃነት ጎን ለጎን ለሥነ ምግባር መርህ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ አማረ፣ የሚዲያ ተቋማትም የሚያስተላልፏቸውን መረጃዎች የሚያጣሩበት ራሱን የቻለ ክፍል ሊያዘጋጁ ግድ ይላቸዋል ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe