ወቅታዊ መግለጫ‹መገናኛ ብዙሃን  የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንቡን በማክበር ተጨማሪ ግጭት እንዳይፈጠር ሙያዊ  ሃላፊነታቸውን...

‹መገናኛ ብዙሃን  የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንቡን በማክበር ተጨማሪ ግጭት እንዳይፈጠር ሙያዊ  ሃላፊነታቸውን  ሊወጡ ይገባል፤›

ለ ሁሉም መገናኛ ብዙሃን

ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

‹መገናኛ ብዙሃን  የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንቡን በማክበር ተጨማሪ ግጭት እንዳይፈጠር ሙያዊ  ሃላፊነታቸውን  ሊወጡ ይገባል፤›

(ሐምሌ  6፤2012 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ  ብዙሃን   ምክር  ቤት   በሥነ  ምግባር   የታነፀ     በሃላፊነት  ስሜት  ህዝብን  የሚያገለግል ሚዲያ  በሀገራችን  እንዲጎለብት የሚሰራ  ሲሆን የመንግስትና  የግል መገናኛ ብዙሃንን፤የማህበረሰብ መገናኛ ብዙህንን እንዲሁም የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራትን በአባልነት ያቀፈ ተቋም ነው፡፡ ምክር ቤቱ  በአሁኑ ወቅት የአርቲስት አጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሀገራችን በተከሰተው ግጭት  የሰው ህይወት በመቀጠፉ የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ሁኔታውን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ  ህዝብና መንግስት እያደረጉ ያሉት ርብርብ ይበል የሚያስገኝ እንደሆነ እናምናለን፡፡

መገናኛ ብዙሃን  ወቅቱን አስመልክተው መረጃዎችን ለህዝብ በሚያደርሱበት ጊዜ በምክር ቤታችን የጸደቀውንና ማንኛውም ጋዜጠኛ ሊከተላቸው የሚገቡ የስነ ምግባር ደንቦችን በማክበር መሆን ይኖርበታል፡፡  የሚዲያ ተቋማት ምንም እንኳ የተመሰረቱበት ፍላጎት፤ አላማ እና የኤዲቶርያል ቁመና ልዩነት ሊኖረው ቢችልም በዚህ ወቅት ግን በተቀናጀ መልኩ የሀገርንና የህዝብን ደህንት በማስቀደም ተጨማሪ ግጭት እንዳይፈጠር በጋራ መቆም እንዳለብን ያምናል፡፡

ከአርቲስት አጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ  ተዓማኒ መረጃ ማቅረብ የሚያስፈለግበት ወቅት ላይ ቢሆንም ዘገባዎችን ከፍ ባለ የሀላፊነት መንፈስ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ሊዘነጋ አይገባም፤ በተለይም መገናኛ ብዙሃን ጦርነትን የሚያነሳሱ፣ ጥላቻን የሚሰብኩ እና ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ የአደባባይ መግለጫዎችን በተመለከተ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት የተደነገጉትን ክልከላዎች ማክበር አለባቸው፡፡ በመሆኑም በዘገባዎቻቸው አንድን ሰው በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካዊ አስተሳሰብን አስመልክቶ ጥላቻን የሚያበረታታ እንዲሁም ንቀትን ወይም መገለልን ሊፈጥር የሚችል ቋንቋን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ በምክር ቤታችን በፀደቀው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ሰፍሯል፡፡

የፕሬስ ነፃነት ከሙያ ስነ ምግባር ጋር የተቆራኘ ነው፤ በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን የጋራ ሰላምንና ወዳጅነትን ለማሳደግ እጅግ የተለየ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከሕዝቦች፣ ከብሔረሰቦች ወይም ከሃይማኖቶች ጋር በተያያዘ በሚነሱ አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች ላይ የሚሠሩ ዜናዎች፣ አስተያየቶች ወይም ሃሳቦችና እውነታዎች በተገቢው ሁኔታ ከተረጋገጡ በኋላ መቅረብ ያለባቸው ሲሆን ትኩረታቸው በመፍትሄው ላይ ሆኖ የሕዝቦችን ትስስር፣ ወዳጅነትና ሰላምን ለማስፈን በሚያስችል መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ በህዝቦች መካከል የመነሳሳት ስሜቶችን ሊፈጥሩ የሚችሉ ፎቶግራፎችን እና ምስሎችን ከማሳተም ወይም ከማሰራጨት መታቀብ አለባቸው፡፡

ችግሩ እንደተከሰተ አብዛኛዎቹ የሀገራችን የሚዲያ ተቋማት በሀላፈነት ስሜት እጅግ ሚዛናዊ ዘገባ እየሰሩ መሆኑን ያስተዋልን ሲሆን፤ ይህም በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል አደራ እንላለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ መረጃዎችን ከታማኝ የዜና ምንጮች ብቻ በመጠቀም መስራት የሚገባ ሲሆን  አደገኛ የሆኑ እና በህዝቦች መሀከል ጥርጣሬ የሚፈጥሩ አሳሳች መረጃዎች ለህብረተሰቡ እንዳይሰራጩ መከላከል  ቸል ሊባል የማይገባ መሆኑን በድጋሚ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

ሐምሌ 6፤2012፤ አዲስ አበባ

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe