ወቅታዊ መግለጫ‹መገናኛ ብዙሃን  የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ለሰላም ዘብ በመቆም  ሙያዊ ...

‹መገናኛ ብዙሃን  የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ለሰላም ዘብ በመቆም  ሙያዊ  ሃላፊነታቸውን  ሊወጡ ይገባል፤›

ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

‹መገናኛ ብዙሃን  የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ለሰላም ዘብ በመቆም  ሙያዊ  ሃላፊነታቸውን  ሊወጡ ይገባል፤›

(ጳጉሜ 4፤2014 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ  ብዙሃን   ምክር  ቤት   በሥነ  ምግባር   የታነፀ     በሃላፊነት  ስሜት  ህዝብን  የሚያገለግል ሚዲያ  በሀገራችን  እንዲጎለብት የሚሰራ  ሲሆን ከ60 በላይ የመንግስትና  የግል መገናኛ ብዙሃን፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙህንን እንዲሁም የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራትን በአባልነት ያቀፈ ተቋም ነው፡፡

ምክር ቤቱ  በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ዳግም ጦርነት ውዱ  የሰው ህይወት በመቀጠፉ የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ሁኔታውን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ  ህዝብና መንግስት እንዲሁም ተፋላሚ ሀይሎች ሊጀምሩ ያቀዱት  የድርድር ሂደት ይበል የሚያስገኝ እንደሆነ እናምናለን፡፡

ዳግም ያገረሸው ግጭት ተባብሶና ሰፍቶ የሚቀጥል ከሆነ ከሰው ልጅ ህይወት መጥፋት በተጨማሪ ለከባድ ሰብዓዊ ቀውስና የንብረት ውድመት የሚያጋልጥ መሆኑ ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የጦርነት ጠባሳ ህያው ምስክር ነው፡፡

በመሆኑም ከጦርነትና ግጭት ትርፍ ሊያገኝ የሚችል የህብረተሰብ አካል ያለመኖሩን ከግምት በማስገባት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተሰንቆ የነበረው የሰላም  ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር የመገናኛ ብዙሃን ስለሰላምና አብሮነት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል እንላለን፤

ሆኖም መገናኛ ብዙሃን  ወቅቱን አስመልክተው የግጭት መረጃዎችን ለህዝብ በሚያደርሱበት ጊዜ በምክር ቤታችን የጸደቀውንና ማንኛውም ጋዜጠኛ ሊከተላቸው የሚገቡ የስነ ምግባር ደንቦችን በማክበር መሆን ይኖርበታል፡፡

የሚዲያ ተቋማት በዚህ ወቅት  በተቀናጀ መልኩ የሀገርና የህዝብ ደህንነት ላይ በማተኮር  እንዲሁም የህዝቦችን ለዘመናት የኖረውን አብሮነት በማስቀደም ተጨማሪ ግጭትና መራራቅ እንዳይፈጠር ተግተው ሊሰሩ የሚገባበት ሰዓት ነው፡፡

ካገረሸው ጦርነት ጋር ተያይዞ ለህዝብ የሚቀርቡ  ዘገባዎችን ከፍ ባለ የሀላፊነት መንፈስ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ሊዘነጋ አይገባም፤ በተለይም መገናኛ ብዙሃን ጦርነቱን የሚያባብሱ፣ ጥላቻን የሚሰብኩ እና ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ የአደባባይ መግለጫዎችን በተመለከተ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት የተደነገጉትን ክልከላዎች ማክበር አለባቸው፡፡ በመሆኑም በዘገባዎቻቸው ማናቸውንም የህብረተሰብ ክፍል በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካዊ አስተሳሰብን አስመልክቶ ጥላቻን የሚያበረታታ እንዲሁም ንቀትን ወይም መገለልን ሊፈጥር የሚችል ቋንቋን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ በምክር ቤታችን በፀደቀው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ሰፍሯል፡፡

የፕሬስ ነፃነት ከሙያ ስነ ምግባር ጋር የተቆራኘ ነው፤ በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን የጋራ ሰላምንና ወዳጅነትን ለማሳደግ እጅግ የተለየ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከሕዝቦች፣ ከብሔረሰቦች ወይም ከሃይማኖቶች ጋር በተያያዘ በሚነሱ አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች ላይ የሚሠሩ ዜናዎች፣ አስተያየቶች ወይም የሚሰነዘሩ ሃሳቦች እውነታዎቹ በተገቢው ሁኔታ ከተረጋገጡ በኋላ መቅረብ ያለባቸው ሲሆን ትኩረታቸው በመፍትሄው ላይ ሆኖ የሕዝቦችን ትስስር፣ ወዳጅነትና ሰላምን ለማስፈን በሚያስችል መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ በህዝቦች መካከል የመነሳሳት ስሜቶችን ሊፈጥሩ የሚችሉ የጦር ሜዳ  ፎቶግራፎችን እና አሰቃቂ ምስሎችን ከማሳተም ወይም ከማሰራጨት መታቀብ አለባቸው፡፡

የሰላም ጥሪዎች  ከሀይማኖት ተቋማት፤ ከሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች፤ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ፤ ከውጭ ሀገራት መንግሥታት፣ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከተመድና ከተለያዩ ወገኖች እየተስተጋባ ባለበት በዚህ ወቅት ተፋላሚ ወገኖች መሳሪያቸውን አውርደው ወደ ንግግር እንዲገቡና እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን መገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል።  ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ለሰላም ዘብ በመቆም  ሙያዊ  ሃላፊነታቸውን  ሊወጡም ይገባል እንላለን፤

ጦርነቱ እንዳገረሸና ግጭቱ እንደተባባሰ  በኃላፊነት ስሜት መረጃዎችን እያስተላልፉ ያሉ የሚዲያ ተቋማት የመኖራቸውን ያህል በህዝቦች መሀከል ጥርጣሬ የሚፈጥሩ አሳሳች መረጃዎችና መላምቶች ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ የኢንተርኔት ሚዲያዎች ተስተውለዋል፤ በዚህ አጋጣሚ መረጃዎችን ከታማኝ የዜና ምንጮች ብቻ በመጠቀም መስራት የሚገባ ሲሆን  አደገኛ የሆኑ እና ለህብረተሰቡ ቢሰራጩ ተጨማሪ ጉዳት የሚፈጥሩ ያልተረጋገጡ መረጃዎች እንዳይሰራጩ መከላከል  ቸል ሊባል የማይገባ መሆኑን በድጋሚ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

ጳጉሜ 4፤2014፤ አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe