ወቅታዊ መግለጫ‹መገናኛ ብዙሃን የህዝብን አንድነት የሚያላሉና ከፋፋይ ንግግሮችንና መግለጫዎችን ከማሰራጨት ሊቆጠቡ  ይገባል›

‹መገናኛ ብዙሃን የህዝብን አንድነት የሚያላሉና ከፋፋይ ንግግሮችንና መግለጫዎችን ከማሰራጨት ሊቆጠቡ  ይገባል›

ወቅታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ

ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/

(መጋቢት 112015 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፤

ምክር ቤታችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘመናት አብሮ በኖረው ህዝብ መሀል አንድነትን የሚሸረሽር፤እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያይ የሚያደርግ ከፋፋይ የሆኑ ንግግሮች፤ መግለጫዎችና ሀሳቦች በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በስፋት ሲሰራጭ ተመልክቷል፤

አንዳንዶቹ አሉታዊ ይዘት ያላቸው ንግሮችና መግለጫዎች በመንግስት ባለስልጣናት፤በፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች፤ በሀይማኖት ሰባኪያንና በምሑራን መደረጉን ስንመለከት መገናኛ ብዙኃን በሕጉ አግባብ ሙያዊ ነፃነታቸውን ተጠቅመው ስራቸውን ከፍ ባለ የኃላፊነት ደረጃ ማከናወን ይኖርባቸዋል ብለን እናምናለን፤

መገናኛ ብዙኃን በሕገ መንግስቱም ሆነ ሀገሪቱ ፈርማ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮሎች መሠረት የሕዝብን  አንድነት የሚንዱ፣ ጥላቻንና ግጭትን የሚያባብሱ ንግግሮችና ድርጊቶችን ማሰራጨት የለባቸውም፡፡ ንግግሮቹ በማንም ይነገሩ በማን  ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሡ፣ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ የሚያደርጉና፣ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መልዕክቶችን ከማሰራጨታቸው በፊት አስፈላጊውን የአርትኦት ስራ ሊሰሩባቸው ይገባል፤

ሀገራችን አስከፊ ከሆነ ጦርነት ወጥታ ሕዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ በጀመረበት በዚህ ወቅት በሃላፊነት ቦታ የተቀመጡ ግለሰቦች የህዝቦችን  አብሮነት በማስቀደም ተጨማሪ ግጭትና መራራቅ እንዳይፈጠር ተግተው ሊሰሩ በሚገባበት ሰዓት አንዱን ሕዝብ መጤ ሌላውን ነባር፤ አንዱን ብሔር ፀረ ሰላም ሌላውን የሰላም ዘብ፤ አንዱን የኃይማኖት ተከታይ ሰላማዊ ሌላውን አመፀኛ አድርጎ መሳልና መከፋፈል በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም፤

መገናኛ ብዙኃን በዘገባዎቻቸው ማናቸውንም የህብረተሰብ ክፍል በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካዊ አስተሳሰብን መሠረት በማድረግ የሚሰጥ/የሚነገር/  ጥላቻን የሚያበረታታ፤ ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ የአደባባይ መግለጫዎችን ፤ ንቀትን ወይም መገለልን ሊፈጥር የሚችል ቋንቋን የሚጠቀሙ እንግዶችን ከመጋበዝ እና ከፋፋይ መግለጫዎችንም በማህበራዊ ሚዲያ ጭምር ከማሰራጨት   መቆጠብ እንደሚገባ በምክር ቤታችን በፀደቀው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ሰፍሯል፡፡

በመሆኑም የፕሬስ ነፃነት ከሙያ ስነ ምግባር ጋር የተቆራኘ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን የጋራ ሰላምንና ወዳጅነትን ለማሳደግ እጅግ የተለየ ኃላፊነት እንዳለባቸው በድጋሚ  ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

መጋቢት 11 ቀን 2015 አዲስ አበባ፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe