(አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ዋና ተግባሩ የሆነውን የ“ግልግል” ዳኝነት አካል አደራጅቶ አቤቱታዎች መቀበል መጀመሩ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከተለያዩ ሚዲያዎች ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠና መርኃ ግብሩ ማጠቃለያ የምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ ምክትል ሰብሳቢ ታምራት ኃይሉ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ ባለፉት ዓመታት የጋዜጠኞችን አቅም ለመገንባት በርካታ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና ተግባር የሆነው የግልግል ዳኝነት አካል ተደራጅቶ ስራ መጀመሩንና አቤቱታዎችም እየተቀበለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የግልግል ዳኝነት ማለት በመገናኛ ብዙሃን ስሜ ጠፍቷል፣ ትክክለኛ ያልሆነ ዘገባ ተሰርቷል እና መሰል ህገ ወጥ ተግባራት ተፈጽሟል የሚል አካል መገናኛ ብዙሃኑን ወይም ጋዜጠኛውን ወደ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አቤቱታ በማቅረብ ተጠያቂ የሚያደርግበት አሰራር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ዋና ተግባር የሆነው የግልግል ዳኝነት አካል 16 ከሕዝብ የተውጣጡ አባላት ያሉት ሲሆን በገለልተኝነት ጉዳዩን የማጣራት ሚናም ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ ይህም የፕሬስ ነጻነት ስነ ምህዳሩን ይበልጥ እንደሚያሻሽለው ተጠቁሟል፡፡
በሚዲያ አማካኝነት ወንጀል ተፈጽሟል የሚሉ አካላት ተጠርጣሪ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞችን ተጠያቂ ለማድረግ አቤቱታቸውን ለምክር ቤቱ እንዲጠቁሙም የምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ ምክትል ሰብሳቢ ታምራት ኃይሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በብርሃኑ አበራ