ዜናለውጭ አገራት ዜጎች የመገናኛ ብዙሃን የባለቤትነት ድርሻ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ እንዲስተካከል ተጠየቀ

ለውጭ አገራት ዜጎች የመገናኛ ብዙሃን የባለቤትነት ድርሻ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ እንዲስተካከል ተጠየቀ

አዲስ አበባ:- የውጭ አገራት ዜጎች የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የ25 በመቶ ድርሻ መያዝ ይችላሉ የሚለው የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ እንዲስተካከል የዘርፉ ባለሙያዎች አሳሰቡ። ካልተስተካከለ አገራዊ ጉዳት እንደሚያስከትልም አመለከቱ::

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ ላይ ትላንት በተካሄደው ህዝባዊ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ታምራት ኃይሉ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ አገራት ዜጎች በመገናኛ ብዙሃን የባለቤትነት ድርሻ ውስጥ የ25 በመቶ ድርሻ ይዘው እንዲገቡ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ ካልተስተካከለ በሀገር ደህንነት ላይ ሥጋት ያስከትላል።

የረቂቅ አዋጁ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ በመገናኛ ብዙሃን በኩል አላማቸውን ሊያስፈጽሙ ለሚፈልጉ አገራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ከወዲሁ ሊስተካከል እንደሚገባ አመልክተው፣ በተለይ ግብጽ እና ሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ የደህንነት አደጋ ሊፈጽሙ የሚችሉ አካላት አንድ አራተኛውን የመገናኛ ብዙሃን ድርሻ በመውሰድ በቀላሉ ሊጠቀሙበት የሚያስችል ክፍተት በመሆኑ ረቂቁን ማስተካከል ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢቢኤስ ቴሌቪዥንን ወክለው የተገኙት አቶ ጥላሁን ሰቦቃ፤ የመገናኛ ብዙሃንን ባለቤትነት በተመለከተ 25 በመቶ ድርሻ ለውጭ ዜጎች በጥቅሉ ከመፍቀድ ይልቅ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀደ ተብሎ በግልጽ መቀመጥ እንደሚገባው ገልፀዋል።

እንደ አቶ ጥላሁን ገለፃ፤ የውጭ አገር ዜጎች በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ሥራ ሊያከናውኑ ቢችሉም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግን ባደጉበት ባህል እና አኗኗር ሥር የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። በመሆኑም ረቂቅ ሕጉ ላይ 25 በመቶ የባለቤትነት መብትን ለውጭ ዜጎች በሚል ለአተረጓጎም ክፍት በሆነ መንገድ ከማስቀመጥ ይልቅ ግልጽ በሆነ ቃል ለትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚል ማስቀመጡ የተሻለ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ የመገናኛ ብዙሃን የባለቤትነት ድርሻን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ አገራትን ዜጎች ከማስገባት ይልቅ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ለይቶ ማሳተፉ ለሀገርም የሚበጅ አካሄድ ነው።

አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከሌላው የውጭ አጋር ዜጋ በተለየ ላደገበት ሀገር ደህንነትና ሰላም የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በሃላፊነት እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው፤ በደፈናው ግን የውጭ አገር ዜጎች ሁሉ በመገናኛ ብዙሃን አንድ አራተኛ ድርሻ ይዘው መሥራት አለባቸው ተብሎ ከተፈቀደ በሀገር ሀብት እና ፀጥታ ላይ የሚያመጣው ኪሣራ ከፍተኛ እንደሚሆን ከወዲሁ ማሰብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በሰጡት ምላሽ እንደገለፁት፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ሆነ የውጭ አገራት ዜጎች በሕግ ደረጃ ኢትዮጵያዊያን ካልሆኑ መካከል ናቸው። ይሁንና የተሻለ ለሀገር ጠቀሜታ አላቸው ተብለው ለሚታሰቡት ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ቅድሚያ ለመስጠት እና ለማሳተፍ በአሠራር ረገድ የሚታዩ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የውጭ አገራት ዜጎችን አስመልክቶ የተነሱ ጥያቄዎችን በረቂቁ ውስጥ አካቶ በይበልጥ ለመመለስ ግን ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር መነጋገር ያስፈልጋል።

እንደ ዶክተር ጌዲዮን ከሆነ፤ በአጠቃላይ መመልከት ከተቻለ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጁ ለጋዜጠኞች እና የተቋማት ባለቤቶች የተሻለ ነፃነት የሚሰጥ እና ይበልጥ የሚያሠራ ነው። ከባለቤትነት መብት፤ ከጋዜጠኞች ተጠያቂነት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን በፍጥነት በማየት ለሁለት ዓመት ተኩል በጥናትና ውይይት ደረጃ የቆየውን ረቂቅ ሕግ በፍጥነት ፀድቆ ወደሥራ እንዲገባ ጥረት ማድረግ ይገባል።

በመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 24 ላይ ባለቤትነትን በተመለከተ የውጭ ዜጎችና ድርጅቶች እንዲሁም የውጭ ዜጎች ከ25 በመቶ ያልበለጠ የአክሲዮን ድርሻ የያዙባቸው ድርጅቶች በየጊዜው የሚወጣ ህትመት እና የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ላይ ከ25 በመቶ ያልበለጠ የባለቤትነት ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ሠፍሯል።

አዲስ ዘመን ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

FOLLOW US

4,545FansLike
4,545FollowersFollow
4,213SubscribersSubscribe