ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን /አስቸኳይ/
(ሚያዝያ 10፤2015 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፤
ምክር ቤታችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ከሕግ አግባብ ውጪ ተይዘው ፤ታፍነውና ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀት ተቋማቱ ላይ ብርበራ የማካሄድ ድርጊቶች በተደጋጋሚ መፈፀማቸውን ተገንዝቧል፤
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/13 አንቀፅ 86 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈፀም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ-ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት ተደንግጓል። ሆኖም የሀገሪቱ ከፍተኛ የሕግ አውጭ አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው ይህ አዋጅ ሀሳብን በነፃነት የመግልፅ መብትን ይበልጥ ለማስፋትና ሙያተኞች በሃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ለማበረታታት ያለመ ቢሆንም ከሕጉ መንፈስ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የዜጎች መብት በፍትሕ አካላት በተደጋጋሚ እየተጣሰ ነው፡፡
በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ጋዜጠኞች በፖሊስ ሲያዙ ብቻ ሳይሆን ፍርድ ቤት ሲቀርቡም በአዋጁ መሠረት ያለመሆኑ ባለሙያዎች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ፤ እንዲሸማቀቁና የፕሬስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ እያደረገው ነው፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት የፍትሕ ስርዓቱ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ያለ ቢሆንም ጋዜጠኞችን በተመለከተ ከሕጉ አግባብ ውጪ የሚፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶችን ለማስቀረት ያለመቻሉ ምክር ቤታችንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚዲያ ፖሊሲም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ እውቅና ተሰጥቶት የተቋቋመው ምክር ቤታችን የዚህ አይነት ጋዜጠኞችን የሚያስጠይቅ ክስ በሚኖርበት ወቅት የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስልት ዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ በመሆኑ የፍትሕ ስርኣቱ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም በሕግ መንግስቱ የተረጋገጠውን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሊያስከብር ይገባል ፡፡ ሆኖም ጋዜጠኞች ከስራቸው ጋር በተያያዘ አይጠየቁ የሚል እምነት የሌለን ቢሆንም ሕግ ተርጓሚው አካል /ፍርድ ቤት/ ጋዜጠኞች ተከሰው ሲቀርቡ በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ መሠረት መከሰሳቸው ግልፅ ሆኖ ሳለ በስራ ገበታቸው ላይ ሆነው ጉዳያቸውን መከታተል እንዳይችሉ እንደማንኛውም ተከሳሽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ በመፍቀድ እንዲታሰሩ ማድረግ በምንም መለኪያ ተቀባይነት የለውም፤ ስለሆነም ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡
በመሆኑም መንግስት የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ተግባራቱ ሁሉ ግን ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በማያጠብና የዜጎችን የዲሞክራሲያው ስርዓት ተሳትፎ በማያቀጭጭ መልኩ ሊሆን ይገባል፤ ማናቸውም ሕግን የማስከበር ተግባራትም በሕግ አግባብ ብቻ መመራት ስላለበት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መሠረት እንዲኖረው የፍትሕ ሥርዓቱ በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ድንጋጌ ብቻ በመመራት ሕገመንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻም የመገናኛ ብዙሃን የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የፍትሕ ስርዓቱ በሕግ በተደነገገው አሰራር ብቻ የሚመሩ ስለመሆኑ ለህብረተሰቡ ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራቸውን አበክረው እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሚያዝያ 9 ቀን 2015 አዲስ አበባ፤